የፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታዎች ውጤት ግምቶች

ታትሟል

ቅዳሜ እና እሁድ የፕሪሚየር ሊግ እና ተጠባቂ የኤፍኤ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በኤፍኤ ዋንጫ ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል እንዲሁም ሲቲ ከ ኒውካስል ግጥሚያ ያደርጋሉ።

የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የጨዋታዎቹን ግምት እንደሚከለው አስቀምጧል።

ዎልቭስ ከ ኮቫንተሪ (ኤፍኤ ካፕ)

ይህን ጨዋታ ቮልቭስ ያሸንፋል ብዬ እገምታለሁ። በሜዳቸው እንደመጫወታቸው በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበለይነት እንደሚይዙ ግምቴ ነው።

ግምት፡ ዎልቭስ 2 - 1 ኮንተሪ

በርንሊ ከ ብሬንትፎርድ (ፕሪሚየር ሊግ)

ከዚህ ቀደም በሰጠኋቸው ግምቶች በርንሊ በሜዳው ቢያንስ አቻ ይለያያል እያልኩ ብገምትም ሁሌም እንደተሳሳትኩ ነው።

አሁንም ቢሆን ባለሜዳዎቹ ጥሩ የግል ማግባት ዕድሎች እንደሚኖራቸው እገምታለሁ። በመጨረሻ ግን ድል ከብሬንትፎርድ ጋር ነው የምትሆነው።

ንቦቹ ጥሩ የሚባል አቋም ላይ ባይገኙም ይህን ጨዋታ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ እገምታለሁ።

ግምት፡ በርንሊ 1 - 2 ብሬንትፎርድ

ሉተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስ (ፕሪሚየር ሊግ)

ይህ ጨዋታ ላለመውረድ ከሚደረጉ ትንቅንቆች አንዱ ይሆናል።

ሉተን በ21 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ፎረስት ደግሞ በ24 ነጥብ 17ኛ ነው።

ሉተን በዚህ የውድድር ዓመት እጅግ አስቆጪ የሆኑ ሁለት ሽንፈቶችን አስተናግዷል። እነዚህም ከስድስት ሳምንታት በፊት በሜዳቸው በሼፊልድ የተሸነፈበት አጋጣሚ አንዱ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ቦርንመዝን 3 ለ 0 መምራት ችለው 4 ለ 3 የተሸነፉበት ሌላኛው ያመለጣቸው ዕድል ነው።

የሉተን ችግር ግብ ማስተናገዱ ነው። በ16 ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ኳስን ከመረብ ማገናኘት የቻለ ቡድን በወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል።

በዚህ ጨዋታ የኑኖ ኤስፒሪቶ ቡድን ይሸነፋል የሚል ግምት የለኝም።

ግምት፡ ሉተን 1 - 1 ፎረስት

ፉልሃም ከ ቶተነሃም (ፕሪሚየር ሊግ)

ባለፈው ሳምንት ቶተነሃም ወደ ቪላ ፓርክ አቀንቶ አስደናቂ ድልን በኡናይ ኤምሪ ቡድን ላይ ተጎናጽፏል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ በዚህ ጨዋታ መፈተኑ አይቀሬ ነው። ቶተነሃም ተከላካዩን ሚኪ ቫን ዲ ቢክን በጉዳት ማጣቱ የተከላካይ መስመሩን ያሳሳዋል።

በተቃራኒው ፉልሃም በሜዳው ጥሩ ቡድን ነው።

ግምት፡ ፉልሃም 2 - 2 ቶተነሃም

ማንቸስተር ሲቲ ከ ኒውካስትል (ኤፍኤ ዋንጫ)

ጋርዲዮላ በኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታዎች ጠንካራ አሰላለፍን ይዞ ሲገባ ነው የምናውቀው። ለዚህ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥም እጠብቃለሁ።

ሲቲዎች ይህን ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የኤፍኤ ዋንጫን እንደሚያነሱ ግምቴ ነው።

ግምት፡ ሲቲ 3 - 1 ኒውካስትል

ቼልሲ ከ ሌስተር (ኤፍኤ ዋንጫ)

ኤፍኤ ዋንጫ ለቼልሲ ትልቅ ትርጉም አለው። ምክንያቱም በፕሪሚየር ሊጉ የዘንድሮ አያያዛቸው የዋንጫ ተፎካካሪ ቀርቶ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነታቸውን የሚያረጋግጥ ቦታ እንኳ ማግኘት አይችሉም።

ስለዚህ ያላቸው አማራጭ የኤፍኤ ዋንጫን ለማንሳት የተቻላቸውን ማድረግ ነው።

ቼልሲ በሜዳው እንደመጫወቱ ሌላ ዕድል ነው።

ቀበሮዎቹ በበኩላቸው የዘንድሮ ዋና ትኩረታቸው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለስ ነው። ሌስተር በዚህ ጨዋታ ቼልሲን መፈተን ቢችም ድሉ የባለሜዳዎቹ ይሆናል።

ግምት፡ ቼልሲ 3 - 0 ሌስተር

ዌስት ሃም ከ አስተን ቪላ (ፕሪሚየር ሊግ)

ሁሉም ክለቦች በሳምንቱ አጋማሽ ቀናት በዩሮፓ እና ኮንፍረንስ ሊግ ጨዋታዎች ነበሯቸው። እነዚህ ግጥሚያዎች የሚፈጥሩባቸውን ጫና የምንመለከተው ይሆናል።

ቪላ ከመዶሻዎቹ በላይ የተሻለ ጥራት አላቸው። ይህንንም በቀደመ ጨዋታ ዌሰት ሃምን 4 ለ 1 ሲያሸንፉ አሳይተዋል።

የኡይን ኤምሪ ቡድን በየትኛውም አጋጣሚ ዕድሎችን መፍጠር የሚችል ቡድን ነው።

ግምት፡ ዌስት ሃም 1 - 2 ቪላ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል

አንድ ጓደኛዬ ይህን ጨዋታ ዩናይትድ እንደሚያሸንፍ ሲነግረኝ በጣም እንደተሳሳተ ነግሬዋለሁ።

ሊቨርፑል በሰሞኑ አቋማቸው ላይ ሆነው ከተገኙ ጨዋታውን ያለጥርጥር እንደሚያሸንፉ ጥያቄ የለውም።

እንደ ሞ ሳላህ ዓይነት ቁልፍ ተጫዋቾች ተመልሰዋል።

ለዩናይትድም የራስመስ ሆሉዩንድ ወደ ሜዳ መመለስ ትልቅ ዜና ነው።

ግምት፡ ዩናይትድ 1 - 2 ሊቨርፑል