ሊቨርፑል ከኒውካስል፤ ፎረስት ከአርሰናል. . . የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ከዋንጫ ፉክክር የተንሸራተተው አርሰናል ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ወደ ድል ይመለስ ይሆን?
ቡድኑ በፉክክሩ ለመዝለቅ ቀሪ ጨዋታዎችን በሙሉ ማሸነፍ እንደሚኖርበት የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ይናገራል።
በሌላ ሳምንቱ መርሃ ግብር ደግሞ በተከታታይ ከባድ ጨዋታዎች በማድረግ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል በሜዳው ኒውካስልን ያስተናግዳል።
ሱተን እነዚህን ጨምሮ በሳምንቱ አጋማሽ የሚከናወኑ ጨዋታዎችን ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ብራይተን ከ በርንመዝ
ብራይተን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ እስከ አምስት ባለው ደረጃ የማጠናቀቅ እድል እንዳለው አሳይቷል።
በርንመዝ ቅዳሜ እለት በዎልቭስ ሲሸነፍ በቀይ ከሜዳ የተባረረውን ዛባርንይን መተካት ይኖርበታል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 1 – 1
ክሪስታል ፓላስ ከ አስቶን ቪላ
እስከ አምስት ባለው ደረጃ ውስጥ የሚያጠናቅቁ ቡድኖች በሚቀጥለው ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ ይሳተፋሉ።
አስቶን ቪላን ጨምሮ ግማሽ ያህሉ የሊጉ ቡድኖች ይህንን ዕድል ማሳካት እንደሚችሉ ያስባሉ።
ፓላስ በሜዳው ጎሎችን እያስቆጠረ አለመሆኑን በ13 ሊግ ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ብቻ ማስቆጠሩ ማሳያ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ቪላ ከሜዳው ውጭ ሲቸገር ተደጋግሞ ታይቷል። ጨዋታው በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል
ግምት፡ 1 – 1
ዎልቭስ ከ ፉልሃም
ማቲየስ ኩኛ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አራት ጎሎችን ከማስቆጠሩም በተጨማሪ ዎልቭስ ከወራጅ ቀጠናው እየራቀ ይገኛል።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ዎልቭስ ፉልሃምን 4 ለ 1 ሲያሸንፍ ብራዚላዊው ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
የማርኮ ሲልቫ ቡድን ከክራቨን ኮቴጅ ይልቅ ከሜዳው ውጭ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል።
በተደጋጋሚ የፉልሃም ውጤት በተቃራኒው እየሆነብኝ መጥቷል። በዚህ ምክንያት ከማስበው በተቀራኒ የሆነ ግምት ለማስቀመጥ ተገድጃለሁ።
ግምት፡ 1 – 2
ቼልሲ ከ ሳውዝአምፕተን
ቼልሲ ባለፉት ጨዋታዎች ደካማ ከመሆኑም ባሻገር በሳምንቱ መጨረሻ አስቶን ቪላን ሲመራ ቆይቶ ለመሸነፍ ተገዷል።
የኤንዞ ማሬስካ ቡድን ወደ ማሸነፍ መመለስ የሚኖርበት ሲሆን ከሳውዝአምፕተን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ደግሞ ጥሩ ዕድል ይፈጥርለታል።
ቅዱሳኖቹ ለሰማያዊዎቹ የሚፈልጉትን ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ቼልሲን መቋቋም አይችሉም።
ግምት፡ 2 – 0
ብሬንትፎርድ ከ ኤቨርተን
ብሬንትፎርድ በተከታታይ ዌስት ሃም እና ሌስተር ላይ ድል አስመዝግቧል። ኤቨርተንም በዴቪድ ሞዬስ ስር ትልቅ መሻሻል አስመዝግበዋል።
የሞዬስ ልጆች ድንቅ ሥራ ቢሠሩም በዚህ ጨዋታ ግን ምንም ነጥብ ማግኘት አይችሉም።
ግምት፡ 2 – 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ኢፕስዊች
በመጀመሪያው የሩበን አሞሪም ጨዋታ ቀያዮቹ ሴጣኖች ወደ ኢፕስዊች አቅንተው አቻ ተለያይተዋል።
ዩናይትድ በሳምንቱ መጨረሻ ጉዲሰን ፓርክ ላይ 2 ለምንም ከመመራት ተነስቶ አቻ መለያየቱ ቢያስወድሰውም አሳማኝ ግን አይደለም።
ኢፕስዊች በበኩሉ በተቶተንሃም 4 ለ 1 ቢሸነፍም በርካታ ዕድሎችን መፍጠር ችሏል። በኦልድትራፎርዱ ጨዋታም በሊያም ዴላፕ ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ።
ሦስት ነጥብ ማግኘት ለኢፕስዊች ትልቅ ውጤት ቢሆንም ጨዋታውን ዩናይትድ ያሸንፋል።
ግምት፡ 2 – 1

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ አርሰናል
ቅዳሜ ዕለት አርሰናል በሜዳው በዌስትሃም መሸነፉ የዋንጫ ተስፋውን አጨልሞታል።
ሦስት ነጠብ ለማሳካት የሚሞክሩበት ጨዋታ ቢሆንም ከፎረስት ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
ፎረስትም በጥሩ አቋም ላይ አይገኝም። ቡድኑ በኒውካስል ከመደቆሱም በላይ ተከላካይ መስመሩ ብዙ ክፍተት እንዳለበት ታይቷል።
ለመድፈኞቹ ማን ኳስና መረብን ያገናኛል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከባድ ይሆናል።
በአጥቂ መስመር ላይ የሚሰለፍ ተጫዋችም ቡድኑ የለውም።
ግምት፡ 1 – 1

ቶተንሃም ከ ማንቸስተር ሲቲ
ይህ ለመገመት ከባድ የሆነ ጨዋታ ነው።
ጨዋታው አስደሳች ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቻልም ግን ሁለቱም ቡድኖች 3 ለምንም ማሸነፍ የሚችሉት ጨዋታ በመሆኑ ለመገመት ይከብዳል።
ሲቲ ጥሩ ባልነበረበት የሊቨርፑል ጨዋታ ብቸኛው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ተጫዋች ዠርሚ ዶኩ ነበር።
ቶተንሃም በበኩሉ 4 ለ 1 ቢያሸንፍም ኢፕስዊች ከፈጠረው ዕድል አንጻር ሲቲም ተመሳሳይ አካሄድ ሊኖረው ይችላል።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ቶተንሃም 4 ለምንም ቢያሽንፍም በዚህኛው ጨዋታ ግምቱን ለሲቲ እሰጣለሁ።
ግምት፡ 1 – 2

ሊቨርፑል ከ ኒውካስል
የአርን ስሎት ቡድን የሲቲን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመቋቋም ማሸነፍ ችሏል።
ሊቨርፑልን ማሸነፍ ከባድ ሲሆን ኒውካስል ደግሞ በውጤት መዋዠቅ ውስጥ ይገኛል።
ኒውካስል ጥሩ ፉክክር ማድረግ ቢችልም ሊቨርፑል ሦስቱን ነጥብ በማሳካት ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ያጠናክራል።
ግምት፡ 2 – 1
ዌስት ሃም ከ ሌስተር ሲቲ
ዌስት ሃም ቅዳሜ ዕለት ከአርሰናል ጋር ጥሩ መከላከል ብቻ ሳይሆን መልሶ ማጥቃትም ችሏል።
አሰልጣኝ ግርሃም ፖተር ድሉን ለማስቀጠል የሚፈልጉ ሲሆን ጃሮድ ቦዌን ደግሞ የፊት መስመሩን በብቃት ይመራላቸዋል።
ይህ በቀላሉ የሚያሽንፉት ጨዋታ ነው።
ሌስተር ከዚህ ጨዋታ ምንም ካለማግኘቱም በላይ በሊጉ የመቆየቱ ነገርም አጠራጣሪ ነው።
ግምት፡ 2 – 0















