ሊቨርፑል በፒኤስጂ ተሸንፎ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውጭ ሆነ

ዳርዊን ኑኔዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መሪው ሊቨርፑል በፈረንሳዩ ፒኤስጂ ተሸንፎ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውጭ ሆኗል።

አንፊልድ የተካሄደው 120 ደቂቃ የወሰደ ፍልሚያ ፓሪ ሳን ዠርማ 1 - 0 አሸንፎ በድምር ውጤት 1 አቻ በመጠናቀቁ ቡድኖቹ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ለማምራት ተገደዋል።

በፍፁም ቅጣት ምቱ የሉዊስ ኤንሪኬ ቡድን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ሊቨርፑል ከውድድሩ ውጭ ማድረግ ችሏል።

ኡስማን ዴምቤሌ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራት ጎል ፒኤስጂ ጨዋታውን ሲመራ ቆይቷል። ሊቨርፑል የፒኤስጂን ተከላካይ መስመር አልፎ ኳስን ከመረብ ለማገናኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቱ የፒኤስጂው ጂያንሉጂ ዶናሩማ ኮከብ ሆኖ አምሽቷል። ዶናሩማ የዳርዊን ኑኔዝ እና ከርቲስ ጆንስ ኳሶችን ሲመልስ ዲዘሬ ዱዌ የመጨረሻዋን ፍፁም ቅጣት ለፒኤስጂ አስቆጥሯል።

ሊቨርፑል ጨዋታው እንደተጀመረ ጎል ለማስቆጠር በሞሐመድ ሳላህ በኩል በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሰካለትም።

ይህ የሊቨርፑል የማጥቃት ጨዋታ ለመልሶ ማጥቃት ዕድል የፈጠረለት ፒኤስጂ በ12ኛው ደቂቃ በዴምቤሌ በኩል የጨዋታው ወሳኝ የሆነችውን ጎል ማግኘት ችሏል።

ዶናሩማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ የቀረበው ሊቨርፑል በሉዊዝ ዲያዝ፣ ጃሬል ኩዋንሳህ እና ዶሚኒክ ስቦዝላይ በኩል ያደረጋቸው ሙከራዎች ከሽፈዋል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ባሉት 30 ደቂቃዎች የፈረንሳዩ ክለብ የተሻለ ሆኖ ቢገኝም አሊሰን የሊቨርፑል ደጀን ሆኖ አምሽቷል።

በሊቨርፑል የመጀመሪያው የውድድር ዘመናቸው ላይ የሚገኙት አርን ስሎት ሶስት ዋንጫዎች ለማንሳት ያለሙት ሕልም በጊዜ ጨልሟል።

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከአርሰናል በ15 ነጥቦች ርቀው የሚመሩት ቀያዮቹ በሚቀጥለው እሑድ በካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ከኒውካስል ይጫወታሉ።

በሌሎች የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዙር 16 የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ባርሴሎና በድምር ውጤት ቤንፊካን 4-1 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።

ባየር ሚዩኒክ ሌቨርኩሰንን በድምር ውጤት 5-0፤ ኢንተር ሚላን ደግሞ ፈይኖርድን 4-1 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው።

ረቡዕ ምሽት በሚደረጉ ጨዋታዎች ሊል ከቦሩሲያ ዶርትመንድ፣ አርሰናል ከፒኤስቪ፣ አስተን ቪላ ከክለብ ብሩግ እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ከሪያል ማድሪድ ይጋጠማሉ።