የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ንብረት የሆነው የግብርና እና ቴክኒክ ትምህርት ቤት በኤርትራ መንግሥት ተወረሰ

ሓጋዝ የግብርናና ቴክኒክ ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, NS

ታትሟል

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውና ሓጋዝ የተሰኘው የግብርና እና ቴክኒክ ትምህርት ቤት በኤርትራ መንግሥት መወረሱን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በላሳል ማህበር የሚተዳደረው ሓጋዝ የግብርናና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ላለፉት 23 ዓመታት በአግሮ መካኒክስ፣ የእንስሳት እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በውሃና አፈር ጥበቃና በመስኖ ልማት ዘርፍ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል።

ትምህርት ቤቱ የሻልኩ ወይን፣ ማርማላት እንዲሁም የወተት ከብቶች፣ እውቅና ያተረፉ እርጎ፣ ሪኮታ አይብ እና ቅቤ በማምረት ለህዝቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበር።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ለመጡና በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑም ተጠቅሷል።

ከዚህ ትምህርት ቤት ሌላ በደቀምሃረ የሚገኘው የካቶሊክ ንብረት የሆነው ዶንቦስኮ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ለመንግሥት እንደሚተላለፍ ተጠቁሟል።

በአውሮፓውያኑ 2019  የኤርትራ መንግሥት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ በሚሶንያውያን፣ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና በእስልምና ሲተዳደደሩ የቆዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እንደወረሰ ይታወቃል።

በዚያው ዓመት በመላ አገሪቱ የሚገኙ የካቶሊክ የጤና ተቋማትን እንደተወረሱም ተገልጾ ነበር።

የኤርትራ መንግሥት እነዚህን ንብረቶች ለመውረስ አዋጅ ቁጥር 73/1ን ይጠቅሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤርትራ መንግሥት እነዚህን ተቋማት ሲወርስ የሃገሪቱ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ  “የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከሕዝብ አገልግሎት ጋር የተሳሰረ ነው፣ የሰው ልጅን ለመገንባት ካልሆነ በቀር ከመንግሥትና ከአገር ጋር ተቃርነን አናውቅም” ሲል በምላሹ ለኤርትራ መንግሥት ጽፎ ነበር።

ጉባኤው የውርስ ውሳኔው በ1982 የደርግ ስርአት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲተዳደሩ የነበሩት ካምቦኒ፣ ላሳለ እና ቅድስት ሃናን ለመውረስ ካደረገው ውሳኔ ጋር ተመሳሳይ ነው ብሏል።

የካቶሊክ ጳጳሳት የኤርትራ መንግሥት ሁሉንም ያሳተፈ ዲሞክራሲያዊ ሃገር እንዲገነባ እና ያለውን አምባገነናዊ የስልጣን አያያዝ እንዲያቆም በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ይሰማል።

በአውሮፓውያኑ 2014 የኤርትራ የካቶሊክ ጳጳሳት በላምፓዱሳ ለተፈጸመው የወጣቶች እልቂት ምላሽ “ወንድምህ የት ነው?” በሚል ሓዋርያዊ መልእክት የኤርትራ ህዝብና መንግሥት ያሉበትን ሁኔታ እንዲመረምርና “ከአምላክ የራቁት ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ እንዲሁም ከህግ የራቀ ወደ ህግ እንዲመለሱ” ጠይቀዋል።

እንዲሁም ከአራት አመታት በፊት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በማድነቅ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲመለሱ እንዲሁም በድንበር ላይ ያሉ ህዝቦችን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩና  ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ ኣቅርበው ነበር።

በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የኤርትራ የፖለቲካ ተንታኞች መንግሥት እየወሰደው ያለው እርምጃ ቤተክርስትያንዋንና እና ሌሎች ሃይማኖቶችን ለማዳከም የወሰደው የበቀል እርምጃ ነው ሲሉ ይገልጹታል።

የሓጋዝ እና የዶንቦስኮ ኣዳሪ የግብርና እና ቴክኒክ ትምህርት ቤቶች ከኤርትራ ነፃነት በኋላ በድህነት እና በመሃይምነት እየተሰቃየ ያለውን ህዝብ ለማገልገል ከተከፈቱት ትምህርት ቤቶች መካከል እንደነበሩ ብዙዎቹ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።