ሩሲያ ወደ ሰላም እንድትመጣ ምዕራባውያን ሊያስገድዷት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ምዕራባውያን መሪዎች “ሁሉንም መንገዶች” በመጠቀም ሩሲያ ወደ ሰላም እንድትመጣ ጫና ሊያደርጉባት እንደሚገባ አሳሰቡ።
ዘለንስኪ በስፔን ባደረጉት ንግግራቸው “ዩክሬንን አጥፍታ ለመቀጠል የምታስበውን” ሩሲያን በተጨባጭ አስገዳጅ ሁኔታ ሊጫንባት ይገባል ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም የሩሲያ ጦር ክሬሚያን ጨምሮ ከተቆጣጠራቸው የዩክሬይን ግዛት ጠቅልሎ እስካልወጣ ድረስ በቀጥታ ከሩሲያ ጋር እንደማይደራደሩ ተናግረው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ሩሲያ ወደ ሰላም እንድትመጣ አጋሮቻቸው እንዲያስገድዷት የተናገሩት ሩሲያ በጦር ግንባር እያሸነፈች እና ዩክሬን ከምዕራባውያን ይለገስላት የነበረው የጦር መሳሪያዎች እጥረት ባጋጠማት ወቅት ነው።
ሩሲያ በየወሩ ወደ 3 ሺህ 200 ቦምቦችን እያዘነበች መሆኑን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ከስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ጋር የተገናኙት ዘለንስኪ “እንዴት ነው ይሄንን የምትዋጉት” በማለት በማድሪድ ጋዜጠኞችን ጠይቀዋል።
ሆኖም ዘለንስኪ በሚቀጥለው ወር በስዊዘርላንድ ሊካሄድ በታቀደው የሰላም ጉባዔ ላይ ሩሲያ ትጋበዝ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።
ጉባዔው ከ90 በላይ አገራት ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ጉባዔ ላይም ፍትህ የሰፈነበት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሩሲያ ከወረረቻቸው ግዛቶች እንድትወጣ፣ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ለደረሰው ጉዳት የካሳ ክፍያ እና የሩሲያ የጦር ወንጀሎችን ለመክሰስ ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋምን ጨምሮ ዩክሬን ባቀረበቻቸው 10 ሃሳቦች ልዑካኑ ይወያያሉ ተብሏል።
የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለውይይት ዝግጁ ናቸው ነገር ግን “በልዩ ወታደራዊ ዘመቻ የተደረሰውን ድል ለማሳካት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በማድሪድ ባደረጉት ንግግራቸው ዩክሬን በሩሲያ ግዛቶች ላይ ጥቃት እንድትፈጸም የተለገሱ የጦር መሳሪያዎች ላይ የተጣለውን እገዳ ምዕራባውያን እንዲያነሱ ጠይቀዋል።
አሜሪካን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን ሃገራት ዩክሬን ጥቃቷን በሩሲያ ግዛቶች ላይ ሳይሆን ዩክሬን ውስጥ ባሉ የሩሲያ ኃይሎች ላይ እንድትወሰን አሳስበዋል።
ከምዕራባውያን አገራት በቢሊዮን ፓውንድ የሚገመት ዕርዳታን እየተቀበለች ያለችው ዩክሬን ከተቀመጠላት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ጦርነቱ እንዴት መቆም እንዳለባት የራሷን አቅጣጫ መንደፍ አንዱ ነው። ለዚያም ነው ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ቀደም ብለው የሩሲያ ጦር ከዩክሬን ግዛቶች ጠቅልለው እንዲወጡ እንዲሁም የሩሲያን የወደፊት ጥቃቶች መከላከል የሚያስችላቸው ዋስትናን ጨምሮ አስር ነጥቦች ያሉት የሰላም እቅድ ያቀረቡት።












