በአሜሪካ የአውሮፕላን ሞተር በኃይል የሳበው የአየር መንገድ ሠራተኛ ሕይወቱ አለፈ

የዴልታ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዴልታ አየር መንገድ አውሮፕላን
ታትሟል

አሜሪካ ቴክሳሰ ውስጥ በሚገኝ አየር ማረፊያ የሚሠራ አንድ ግለሰብ የመንገደኞች አውሮፕላን የሞተር ኃይል ስቦ ካስገባው በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ።

ሠራተኛው በዴልታ አየር መንገድ አውሮፕላን ሞተር ኃይል ተጎትቶ የገባው፣ የአውሮፕላኑ አንደኛው ሞተር ብቻ እየሰራ መሬት ላይ በዝግታ እየተጓዘ ባለበት ጊዜ መሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የሟቹ ሠራተኛ ቀጣሪዎች እንዳሉት በክስተቱ ዙሪያ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ አደጋው ከጥንቃቄ ጉድለት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አመልክቷል። ነገር ግን አደጋው እንዴት እንደተከሰተ አስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም።

የሚመለከተው የአሜሪካ መንግሥት ተቋምም አደጋው የደረሰበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ነው።

በዚህም መሠረት የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ከዴልታ አየር መንገድ ጋር ግንኙነት ማድረጉን አመልክቶ “ጉዳዩ በመረጃ ስብሰባ ሂደት ላይ” መሆኑ ተገልጿል።

አደጋውን ያደረሰው ኤርባስ ኤ319 የተባለው አውሮፕላን ከሎስ አንጀለስ ተነስቶ ሳን አንቶኒዮ የደረሰው አርብ ምሽት ላይ ነበር።

ባለሥልጣናት አስካሁን ድረስ በአደጋው ሕይወቱ ያለፈውን የአየር መንገዱ ሠራተኛ ማንነትን አልገለጹም።

ነገር ግን ሟች በአየር ማረፊያው ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን እንዲሰራ በዴልታ አየር መንገድ ኮንትራት የተሰጠው ድርጅት ባልደረባ መሆኑ ተገልጿል።

ኮንትራት የወሰደው ድርጅት እንዳለው “ባደረግነው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ አደጋው በአየር ማረፊያው ውስጥ ከምናካሂደው የሥራ ሂደት እና የጥንቃቄ መመሪያ ጋር የሚገናኝ አይደለም” ብሏል።

የዴልታ አየር መንገድ ቃል አቀባይ እንዳሉት አየር መንገዳቸው በደረሰው አደጋ ማዘኑን በመግለጽ “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሟቹ ግለሰብ ቤተሰቦች እና ወዳጆች ጎን ይቆማል” ብለዋል።

አየር መንገዱ ለአንድ የመገናኛ ብዙኃን እንዳለው የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት የአደጋውን ምክንያት ለማወቅ ምርመራቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ አብሮ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ከስድስት ወራት በፊት አላባማ ግዛት ውስጥ የአንድ የአየር ማረፊያ ሠራተኛ ሕይወት በተመሳሳይ ሁኔታ ያለፈ ሲሆን፣ በተደረገው ምርመራ አደጋው ፔድሞንት በተባለው የአካባቢ አየር መንገድ የደኅንነት ጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት የሥራ ቦታ ደኅንነት እና ጤንነትን የሚከታተለው መንግሥታዊ ተቋም ለደረሰው ጉዳት አየር መንገዱ የ15,625 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ጥሎበታል።

ተቆጣጣሪው አካል እንዳለው “ተገቢው የደኅንነት አጠባበቅ መመሪያ ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ የሰው ሕይወት የቀጠፈውን አደጋ ማስቀረት ይቻል ነበር” ብሏል።