የዩክሬን ኒውክሌር ማበልፀጊያ ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ታትሟል

የዩክሬን የኒውክሌር ማበልፀጊያ በድሮን መመታቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የአቶሚክ ቦምብ ተቆጣጣሪ “የኒውክሌር አደጋ” ሊደርስ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

ሩሲያ ከጥቃቱ ጀርባ ያለችው ዩክሬን ናት ስትል ትወቀሳለች። ዩክሬን ይህን ወቀሳ ታስተባብላለች። በጥቃቱ ሶስት ሰዎች ተጎድተዋል።

ስድስት ማብላያዎች ያሉት ዛፖሪዥዢያ የተሰኘው የዩክሬን ግዙፍ የኒውክሌር ማበልፀጊያ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ይገኛል።

የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ መሰል ጥቃቶች አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ እሑድ ዕለት የደረሰው የድሮን ጥቃት “ግድየለሽ” ነው ብለው “የኒውክሌር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል” እንደሆነ ተናግረዋል።

ደቡብ ዩክሬን የሚገኘው ይህ የኒውክሌር ማበልፀጊያ በአውሮፓው ግዙፉ ነው። ሩሲያ የካቲት 2022 ዩክሬንን ከወረረች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው ይህን ማበልፀጊያ በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው።

በዚህ ማበልፀጊያ የሚሠሩ የኤጀንሲው ባለሙያዎች ማበልፀጊያው “አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት” አረጋግጠው በተለይ አንደኛው ማብላያ ተመትቷል ብለዋል።

ሩሲያዊያን የማብልፀጊያው አስተዳዳሪዎች ደግሞ ከማበልፀጊያው የሚወጣው “ራዲየሽን” ከሌላው ጊዜ የተለየ አለመሆኑን አሳውቀው ለጊዜው ምንም አስጊ ጉዳት የለም ሲሉ ገልጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታቱ ኤጀንሲ ማበልፀጊያው ላይ የደረሰው ጥቃት የኒውክሌር ደኅንነትን አደጋ ላይ እንዳልጣለ ቢያረጋግጥም ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ግሮሲ በዚህ ማበልፀጊያ ላይ “ቢያንስ ሶስት ቀጥተኛ ጥቃቶች ተፈፅመዋል” ብለዋል።

“ይህ ሊሆን አይገባም” ያሉት ኃላፊው “ማንም የኒውክሌር ማበልፀጊያን በመምታት ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅም ሊያገኝ አይችልም። ይህን አንፈቅድም” የሚል ንግግር አሰምተዋል።

ሩሲያ እና ዩክሬን ይህን ማበልፀጊያ በመምታት እና አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ እርስ በርስ ይወቃቀሳሉ።

የማበልፀጊያው ሩሲያዊ አስተዳዳሪ የዩክሬን ጦር ሠራዊት ከጥቃቱ ጀርባ አለ ሲሉ ዩክሬን ግን ይህን ወቀሳ ታስተብላለች።

ባለፈው ወር የኤጀንሲው ባለሙያዎች ለአንድ ሳምንት ያክል በየቀኑ ፍንዳታ ይሰሙ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።