ክብርት ኢልሃን ኦማር ከአሜሪካ ምክር ቤት ቁልፍ የኮሚቴ አባልነት ተባረሩ

ኢልሃን ኦማር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢልሃን ኦማር ከመጀመርያዎቹ ሙስሊም የምክር ቤት አባላት አንዷ ናቸው
ታትሟል

የሜኔሶታ ግዛት ተመራጭ የተከበሩ የምክር ቤት አባል ኢልሃን ኦማር ወሳኝ ከሚባል የምክር ቤት የኮሚቴ አባልነት ተባረሩ።

ኢልሃን ከውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባልነት የተባረሩት በሪፓብሊካኖች ነው።

የተከበሩ የምክር ቤት አባል ኢልሃን ኦማር ለመባረር ያበቃቸው ከዓመታት በፊት በእስራኤል ላይ ሰነዘሩት በተባለ ‘ያልተገባ’ አስተያየት ነው።

በአማካይ ዘመን የአሜሪካ ምርጫ በድጋሚ ያሸነፉት ኢልሃን ኦማር የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባል ናቸው።

ሪፐብሊካኖች ኢልሃን ከውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ መባረራቸው 'ጸረ አይሁድ' ለሆኑት ሁሉ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ዲሞክራቶች በሰጡት ምላሽ ይህ እርምጃ ከሁለት ዓመት በፊት ዲሞክራቶች በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ በነበራቸው ሰዓት ሁለት የሪፐብሊካን እንደራሴዎች በተመሳሳይ ከቋሚ ኮሜቴ አባልነት መባረራቸውን ለመበቀል የተወሰደ ነው።

ኢልሃን ኦማር በበኩሏ እርምጃው አንድም ሙስሊም ሴት በመሆኔ፣ እንዲሁም ወደ አሜሪካ ምድር በስደተኝነበት በመምጣቴ የተቃጣብኝ ነው ብለዋል።

በአማካይ ዘመን ምርጫ ሪፐብሊካኖች ከምክር ቤቱ መቀመጫ አብላጫውን መያዝ ችለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሪፐብሊካን እንደራሴዎች በታችኛው ምክር ቤት 222 መቀመጫን ይዘዋል። የዲሞክራቶች ቁጥር 212 ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የታችኛው ምክር ቤትን ሪፐብሊካኖች መቆጣጠራቸውን ተከትሎም ናንሲ ፒሎሲን ለመተካት ከወራት በፊት የአፈ ጉባኤ ምርጫ ተደርጎ ነበር።

በአሜሪካ የመቶ ዓመት ታሪክ ባልታየ ሁኔታ የተራዘመ ሂደትን ተከትሎ ኬቨን ማካርቲ አሸንፈዋል።

አፈ ጉባኤ ኬቨን ማካርቲ ይህን የአፈ ጉባኤነት ድምጽ ለማግኘት የምክር ቤቱን ነጭ አክራሪ ቀኝ ዘመም የምክር ቤት አባላትን ማባባል ነበረባቸው።

ሪፐብሊካኑ ማካርቲ እጅግ ከተራዘመ ድርድርና ማባበል በኋላም ነው የአፈ ጉባኤነት መዶሻ ለመያዝ የበቁት።

ይህ ሁኔታ ምክር ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ ፍጥጫን አስከትሏል።

ማካርቲ በኢልሃን ኦማር ጉዳይ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ባደረጉት ንግግር ኢልሃን ኦማር በእስራኤል ላይ ከሰነዘሩት አስተያየት አንጻር በፍጹም ቁልፍ በሚባለው የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ መቆየት አልነበረባቸውም።

ኢልሃን ኦማር በ2019 እስራኤል የአሜሪካንን ፖለቲካ በገንዘብ ኃይል እንደምትዘውር የሚያመላክት አስተያየት ከሰጡ በኋላ ናንሲ ፒሎሲና ሌሎች ዲሞክራቶች ሳይቀር ከፍተኛ ትችት ሰንዝረውባቸው ነበር።

እርሳቸውም በኋላ ላይ ይቅርታን ጠይቀው ነበር።

ይሁንና የኢልሃን ይቅርታ ሪፐብሊካኖች በእርሳቸው ላይ ጥርስ መንከሳቸውን አላስቆመም።

በትናንቱ ጉባኤ የኦሃዮ እንደራሴ ማክስ ሚለር ናቸው ኢልሃን ኦማር ከኮሚቴው እንዲባረሩ ምክረ ሐሳብ ያቀረቡትና የጸደቀላቸው።

ማክስ ሚለር የተከበሩ የምክር ቤት አባል ኢልሃን ከኮሚቴው ከተባረሩ በኋላ በሰጡት አስተያየት “የኢልሃን መባረር ተገቢም አስፈላጊም ነበር” ሲሉ በውሳኔው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካንን የፓርቲ ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች ግን የኢልሃን ከኮሚቴው መባረር በሕግ መምሪያው ምክር ቤት ውስጥ የዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን ከፍተኛ ፍጥጫ እንዳለና ይህም በፖርቲ መስመር ተሰልፎ መቆራቆሱ እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ይላሉ።

ኢልሃን ኦማር በሜኔሶታ አንድ የምርጫ ጣቢያ ተወዳድረው በድጋሚ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት የተመረጡ ሲሆን ወደ አሜሪካ በስደት የገቡት በ1990ዎቹ መጀመርያ ነበር።

ኢልሃን በ2018 በአሜሪካ በምክር ቤት አባልነት ለመመረጥ ከቻሉ የመጀመርያዎቹ ሙስሊም አንዷ ለመሆንም በቅተዋል።

ኢልሃን ኦማር በሪፐብሊካን በተለይም ሙስሊምና ስደተኛ ጠል በሆኑ የቀኝ አክራሪ ትራምፕ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻን አትርፈዋል።

የትራምፕ ደጋፊዎች በፖለቲካ ሰልፎች ላይ “ወደመጣችበት ስደዷት” (send her back) የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደነበረ አይዘነጋም።

ኢልሃን ኦማር የተወለዱት በሶማሊያ ሞቃዲሹ ከተማ ነው።