በምሥራቃዊ ኢየሩሳሌም በአንድ ምኩራብ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 7 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምሥራቃዊ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኝ የአይሁዳውያን ምኩራብ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች በጥይት ሲገደሉ ቢያንስ ሦስት ደግሞ ቆስለዋል።
ይህም ከዓመታት በኋላ ያጋጠመ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ነው ተብሏል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በኢየሩሳሌን ከተማ ውስጥ ኔቬ ያኮቭ በተባለ ሰፈር ውስጥ ምሽት ሁለት ሰዓት ከሩብ አካባቢ ነው።
ፖሊስ ጥቃቱ የተፈጸመው “በሽብርተኛ” መሆኑን ገልጾ፣ ፈጻሚው ላይ “እርምጃ ተወስዶበታል” ብሏል።
የእስራኤል የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጥቃት ፈጻሚው ከምሥራቅ ኢየሩሳሌም የመጣ ፍልስጤማዊ ግለሰብ መሆኑን ዘግበዋል።
የእስራኤል ፖሊስ ኮሚሽነር ኮቢ ሻብታይ በጥቃቱ ስፍራ ላይ ሆነው እንደተናገሩት “በቅርብ ዓመታት ካጋጠሙን አስከፊ ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው” ብለዋል።
በምኩራቡ ውስጥ እስራኤላውያን ምዕመናን የአይሁድ ሰንበት መጀመሪያ ላይ ተሰባስበው በነበረበት ጊዜ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። ፖሊስ እንዳለውም ጥቃት ፈጻሚው በጥይት ተመትቶ ተገድሏል።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች የተፈጸመውን ጥቃት ቢያደንቁም፣ ነገር ግን ከአባሎቻቸው አንዱ ስለመፈጸሙ ኃላፊነት አልወሰዱም። በዌስት ባክን እና በጋዛ ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንም ጥቃቱን ደግፈውታል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በናዚዎች የዘር ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸውን ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዶች እና ሌሎች ሰዎች በሚታሰቡበት ዕለት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጥቃቱን ተከትሎ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥቃቱን አጥብቀው በማውገዝ ከእስራኤል ጋር በአንድነት እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
ከጥቃቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እንዲሁም አወዛጋቢው ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ግቪር በስፍራው ተገኝተዋል።
ሐሙስ ዕለት በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ጄኒን ውስጥ እስራኤል በወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ 9 ታጣቂዎች እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ውጥረት ነግሷል።
ይህንንም ተከትሎ ከጋዛ አካባቢ ወደ አስራኤል የሮኬት ጥቃት የተሰነዘረ ሲሆን፣ በምላሹም እስራኤል የአየር ጥቃት ፈጽማለች።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእስራኤል እና በወረራ በተያዘው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ እየተባባሰ ያለው ሁኔታ በጣሙን እንዳሳሰባቸው በቃል አቀባያቸው በኩል ገልጸዋል።
እስራኤል በ1967 (እአአ) በተካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረች በኋላ ዋና ከተማዋ እንደሆነች ብትገልጽም፣ በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅናን አላገኘችም።












