ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ግምት፡ አርሰናል እና ዩናይትድ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ድል ይቀናቸው ይሆን?
በጉጉት የሚጠበቀው የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት ይጀመራል።
የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ ወደ በርንሌይ የሚያቀናበት ጨዋታ የውድድር ዓመቱ የመክፈቻ ጨዋታ እንዲሆን ቀጠሮ ተይዞለታል።
ያለፈውን ውድድር ዓመት የሊጉን ጨዋታዎች ሲገምት የነበረው የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ዘንድሮም 380 የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች ይገምታል።
ዛሬ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ የሚከናወኑትን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎችም እንደሚከተለው ገምቷል።
አርብ
በርንሊ ከ ማንቸስተር ሲቲ
ማንቸስተር ሲቲዎች በኮሙኒቲ ሺልድ ጨዋታ ወቅት ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ አይመሰሉም ነበር። ሲቲዎች ቀዝቀዝ ብለው መጀመር እና አጨራረሱን ማሳመር ተክነውበታል።
እያወራን ያለነው ስለሻምፒዮኖቹ እና ኮከቦችን ስላቀፈው ቡድን ነው።
ብዙዎች በርንሊዮች በሊጉ ይቆያሉ ቢሉም ከሚወርዱት ቡድኖች መካከል እንደሚሆኑ እጠብቃለሁ።
ባለፈው ዓመት በሻምፒዮንሺፑ የቪንሰንት ኮምፓኒ ቡድን ያሳውን አጨዋወት ብወደውም በተመሳሳይ መልኩ በሊጉ ለመጫወት ይከብዳቸዋል ብዬ አስባለሁ።
በዚህ ጨዋታ ላለፉት ስድስት ጨዋታዎች ለሲቲ ጎል ማስቆጠር ያልቻለው ኧርሊንግ ሃላንድ ወደ ጎል አግቢነቱ የሚመለስበት ነው።
ግምት፡ 0 – 2
ቅዳሜ
አርሴናል ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ኖቲንግሃም ፎረስት ባለፈው ዓመት ከሜዳው ውጭ ደካማ ውጤት ያስመዘገበ ቡድን ነው።
አሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐር ቡድኑ እንዳይወርድ ጥሩ ሥራ ቢሠሩም እንደአምናው ዘንድሮ ቡድኑን ለማጠናከር ወደ ገበያ በስፋት አልወጡም።
ያለአጥቂው ጋብርኤል ጂሰስ ወደ ሜዳ የሚገባው አርሴናል ክፍተቱን በአዲሱ ፈራሚ በካይ ሃቨርትዝ የሚሞላ አይመስልኝም።
የማይክል አርቴታ ቡድን የውድድር ዓመቱን በጠንካራ መልኩ ለመጀመር ይፈልጋል።
ግምት፡ 3 – 0
በርንመዝ ከ ዌስት ሃም
አዲሱ የበርንመዝ አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ በነበራቸው አጭር ጊዜ ውስጥ የሚመርጡትን ማጥቃትን መሠረት ያደረገ አጨዋወት ስለመተግበራቸው የሚታይ ይሆናል።
በዝውውር መስኮቱ ያልተንቀሳቀሱት ዌስት ሃሞች አሁን ተጫዋቾችን ለማስፈረም እየሞከሩ ነው።
ዴክላን ራይስን ቀደም ብለው ለአርሴናል ቢሸጡም አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ በሚፈልጉት መልኩ ቡድኑ ተጫዋቾችን አላስፈረመም።
ከማጥቃት ይልቅ መልሶ ማጥቃትን የሚመርጡ ይመስላል።
ግምት፡ 1 – 1
ብራይተን ከ ሉቶን
ሉቶኖች በዝውውር መስኩ ከሚገባው በላይ ለመንቀሳቀስ አልሞከሩም።
አሰልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ ቡድናቸው በሽግግር እና በመልሶ ማጥቃት ላይ የተነሰረቱ ተጫዋቾችን ማምጣታቸውን አስታውቀዋል።
አሌክሲ ማክ አሊስተር እና ሞሰስ ካሲዬዶን የሸጡት ብራይተኖች የባለፈው ዓመት ጥንካሬያቸውን ለመድገም ይቸገራሉ።
የሮቤርቶ ዲ ዜብሪ ቡድን ተጭኖ የሚያጠቃቸውን ቡድን ቢመርጡም ሉቶን ይህንን አያደርግም።
ግምት፡ 2 – 0
ኤቨርተን ከ ፉልሃም
የኤቨርተን ውድድር ዓመት የሚወሰነው ጉዳት በሚደጋግመው ዶምኒክ ክላቨርት-ሌዊን ብቃት ነው።
አስተማማኝ ጎል አስቆጣሪ ስለሌላቸው በዚህ ረገድ ሊረዳቸው ይገባል።
የፉልሃሙ አጥቂ አሌክሳንዳር ሚትሮቪች ወደ ሳዑዲ ለመሄድ ያደረገው ሙከራ ባይሳካም ስለመቆየቱ እርግጠኝነት የለም።
የሞራል መነሳሳቱ ከፍ ያለ ሚትሮቪችን እንመለከታለን ወይስ በጭራሽ ላናየው እንችለላን?
ግምት፡ 1 – 1
ሼፊልድ ዩናይትድ ከ ክሪስታል ፓላስ
ሼፊልዶች ወደ ሊጉ ካደጉ በኋላ ትልልቅ ተጫዋቾቻቸውን ሸጠዋል።
የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ተጫዋቾችን ሊያመጡ ቢችሉም የእስካሁኑ እንቅስቃሴያቸው አጥጋቢ አይደለም።
ትልቁ ተጫዋቸው ዊልፍሬድ ዛሃን ያጡት ፓላሶች ኤቤሬቺ ኤዜ እና ማይክል ኦሊሴ ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል።
ጨዋታውን ፓላሶች እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።
ግምት፡ 0 – 1
ኒውካስል ከ አስቶን ቪላ
ኒውካስል ከባዱ ፈተና ፕሪሚር ሊግ እና ቻምፒዮንስ ሊግ እየተጫወቱ ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑ ነው።
አስቶን ቪላዎች በኡናይ ኤምሬ ስር ለዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግን ድል ይጠበቃሉ።
ይህ ጥሩ ጨዋታ የሚሆን ሲሆን ኒውካስል እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 – 1
እሑድ
ብሬንትፎርድ ከ ቶተንሃም
የሃሪ ኬን ዝውውር ጉዳይ ለአዲሱ አሰልጣኝ አንጂ ፖስትኮግሉ ፈተና እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል።
አሰልጣኙ በማጥቃት ላይ በተመሠረተ አጨዋወታቸው ይታወቃሉ።
በቅጣት ያለአትቂያቸው ኢቫን ቶኒ የሚቀርቡት ብሬንትፎዶች አይደለም ላተዘጋጀ ለተዘጋጀ ቡድንም አስቸጋሪዎች ናቸው።
እንደቆሙ ኳሶች እና የመልስ ውርወራ ያሉ ጥቃቅን ሁነቶች የቶማስ ፍራንክን ቡድን ይወስኑታል።
ግምት፡ 2 – 1
ቼልሲ ከ ሊቨርፑል
ከዚህ ጨዋታ በተለይም ከቼልሲ ምን እንደሚጠበቅ ለመገመት የሚያስቸግረኝ ጨዋታ ነው።
አዲስ ፈራሚው ክሪስቶፈር ንኩንኩ መጎዳቱ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ ዕድለኛ ባያደርጋቸውም ሁለቱም ቡድኖች አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም መጣራቸው ይጠበቃል።
ከስታምፎርድ ብሪጅ የለቀቁ ተጫዋቾች ቢኖሩም አሁን በርካታ ድንቅ ተጫዋቾች አሏቸው። ጥያቄው ፖቸቲኖ በምን ያህል ጊዜ ቡድናቸው ያቀናጃሉ የሚለው ነው።
የሊቨርፑል ደካማው ክፍል ተከላካዩ ሲሆን አጥቂዎቹ ደግሞ ብዙ ጎሎችን ያስቆጥራሉ። በሁለቱም ቡድኖች ጎሎች ይቆጠራሉ።
ግምት፡ 2 – 3
ሰኞ
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ዎልቭስ
ዎልቭስ አሰልጣኙን ባለቀ ሰዓት ከማሰናበት ቀደም ብሎ ቢለያይ የተሻለ ነበር።
አዲስ የተሾሙት ጋሪ ኦኔል ባለፈው ዓመት በበርንመዝ ጥሩ ሥራ ቢያከናውኑም ይህ ግን አዲስ ፈተና ነው።
በዝውውር መስኮቱ ካደረጉት ተሳትፎ በኋላ ማንቸስተር ዩናይትዶች ዘንድሮ የሚኖራቸውን ለውጥ ለማየት ጓጉቻለሁ።
ቡድኑ ከሲቲ ጋር ለዋንጫው የሚፎካከር አይመስለኝም።
አዲሱ ፈራሚ ራስመስ ሆይለን በጉዳት በዚህ ጨዋታ አለመሰለፉ አሳዛኝ ነው።
ግምት፡ 2 – 0