‘ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ገብቷል’ ተመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ተዘፍቋል ሲል ገለጸ።
ለዚህ ከፍተኛ ቁጥር መድረስ ሁነኛው ምክንያት በዓለም ላይ ጦርነት መበራከት፣ ኑሮ መወደድና የአየር ንብረት ለውጥ ናቸው ብሏል።
በድምሩ አሁን ላይ 50 ሚሊዮን ሕዝብ በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ነው ያለው ይላል ድርጅቱ።
ይህ ማለት ከ150 የዓለም ሕዝብ አንዱ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በባርነት ውስጥ ነው።
ዘመናዊ ባርነት ከሚባሉት ውስጥ የአስገዳጅ ጉልበት ብዝበዛ እና ያለ ፈቃድ በትዳር መቀፍደድ ይገኙበታል።
የዓለም አቀፉ ሠራተኞች ድርጅት ነገሮች አሁን እየሄዱበት ያለበት ሁኔታ አስደንጋጭ ነው ይላል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጋይ ራይደር እንደሚሉት የማያቋርጥ የመብት ጥሰቶች ለመፈጸማቸው ምንም አይነት ማስተባበያ ማቅረብ አይቻልም።
“ምን መደረግ እንዳለበት ይታወቃል። በጋራ ለአንድ ዓላማ መነሳት ነው ያለበትን። የንግድ ማኅበራት፣ ቀጣሪዎች፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ እንዲሁም ተርታው ማኅበረሰብ በሙሉ በቅንጅት ሚናውን ሊወጣ ይገባል’ ብለዋል።
ድርጅቱ እንደሚለው ዘመናዊ ባርነት አሁን ላይ እንደታየው የድሃ አገራት ችግር ብቻ አይደለም።
ከግማሽ በላይ የጉልበት ብዝበዛ የሚፈጸመው አድገዋል በሚባሉት የምዕራብ አገራት ውስጥ ነው።
እንደ ጉልበት ብዝበዛም ሆነ ያለ ፈቃድ በትዳር ውስጥ መቀፍደድ በመካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥም የሚስተዋል ችግር ነው።
ሰዎች ያለ ፈቃዳቸው በፍርሃት፣ በጦርነት፣ በነውጥ፣ በመታለል እና አደጋ ይደርስብኛል ብለው በመስጋት በትዳርና ጉልበት በሚበዘብዝ ሥራ ውስጥ ይቆያሉ።
ብዙውን ጊዜ የጉልበት ብዝበዛዎች ለዓመታት የሚቆዩ ሲሆን አስገዳጅ ትዳር ግን በብዛት የዕድሜ ልክ ብዝበዛ ሆኖ ይቀጥላል ይላል ድርጅቱ።
አሁን ላይ አሐዞች እንደሚያሳዩት 27.6 ሚሊዮን ሕዝብ በግዳጅ ሥራ ውስጥ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 3.3 ሚሊዮኑ ሕጻናት ናቸው።
ከነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ደግሞ በወሲብ ንግድ ውስጥ እየተበዘበዙ ነው።
በሌላ በኩል 22 ሚሊዮን ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት በግዳጅ ትዳር ውስጥ እየኖረ ነው። ከዚህ ውስጥ ሁለት እጅ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ትዳሩ ያለ ፈቃድ ጋብቻ ሲፈጸም ዕድሜያቸው 15 እና ከዚያም በታች ነው።
ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በምጣኔ ሃብት ቀውስ ማስከተሉን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ወደዚህ ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ገብተዋል ብሏል ድርጅቱ።
ይህም የሆነው በርካታ ሰዎች ገቢያቸው በመመናመኑና ዕዳ ውስጥ በመዘፈቃቸው ከዚያ የዕዳ አዙሪት ለመውጣት በሚያደርጉት ተጋድሎ ነው።
በሌላ በኩል በበርካታ የዓለም ክፍሎች የተቀሰቀሱ ጦርነቶች እና የአየር ንብረት ለውጥም ሕዝብን ወደ ችጋር እና ብዝበዛ ከቷል።
ድርጅቱ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩን ለመቅረፍ ከልቡ መነሳት እንዳለበት በብርቱ አሳስቧል።












