የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን አወጁ  

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ አገሪቷን ሊመሩ ነው።

ዢ ዢንፒንግ የቻይናው ገዥ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ባደረገው ጉበኤ ዋና ጸሓፊ አድርጎ መምረጡን ተከትሎም ነው ለሶስተኛ ጊዜ ስልጣናቸው የተራዘመው።

የፓርቲው ዋና ጸሃፊ በሃገሪቱ የመሪነት ቦታ የሚያስገኝ ሲሆን መጋቢት በሚደረገውም የብሄራዊ ህዝቦች ጉባኤ በይፋ ስልጣናቸው ይጸድቃል።

ፓርቲው በተጨማሪም 25 አባላት ያሉትን የፖሊት ቢሮ እንዲሁም ሰባት አባላት ያሉትን ቋሚ የፖሊት ቢሮን መርጧል።

ፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውንም ያስተዋወቁ ሲሆን ከነዚህም መካከል የቀድሞው የሻንጋይ ፓርቲ መሪ ይገኙበታል። ሊ ኪያንግ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ይሆናሉ።

ዢ ጂንፒንግ በዛሬው ዕለት አዲሱን የፖሊት ቢሮ ቋሚ ኮሚቴንም እየመሩ ወደ መድረክ መጥተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለመገናኛ ብዙኃንም ፓርቲያቸው በትናንትናው ዕለት ያደረገውን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዳጠናቀቀና ገልጸው “ጥንካሬያችንን በማሰባሰብ በአንድነት ወደፊት እንቀጥላለን” ብለዋል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉባኤውን በከፍተኛ ፍላጎት ሲከታተል መቆየቱን ጠቅሰው የሀገር መሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክትና ደብዳቤ መላካቸውን በመግለጽ ለሁሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከዚያም አዲሱን የፖሊት ቢሮ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በማስተዋወቅ “ሁሉንም በደንብ ታውቋቸዋላችሁ” በማለት ተናግረዋል።

ዢ ሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን አውጀው አዲሱ የአመራር ቡድናቸውን ካስተዋወቁ በኋላም ንግግር አድርገዋል።

በዚህ ንግግራቸው ቻይናን የምትመራበት አቅጣጫ በተመለከተ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ሃገሪቱ ለአለም ኢኮኖሚ በሯን እየዘጋጀች ነው የሚል ስጋት በጨመረበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ “ ቻይና ያለተቀረው አለም ማደግ አትችልም እናም አለምም ቻይናን ይፈልጋል” ብለዋል።

አክለውም “ከአርባ ዓመታት በላይ ባደረግነው የለውጥ እንቅስቃሴ ሁለት ተአምራትን መፍጠር ችለናል። ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ማህበራዊ መረጋጋት ነው” ብለዋል