ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሲሪላንካ ፓርላማ የሕዝብ ድጋፍ የሌላቸውን ፖለቲከኛ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመ
የሲሪላንካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ራኒል ዊክርሜሲንግህ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመ።
ዊክርሜሲንግህ ፕሬዝዳንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት የቀድሞ ፕሬዝደንት አገር ጥለው መሸሻቸውን ተከትሎ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ነበሩ። ከዚያ በፊት ደግሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
ግለሰቡ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው በአገሪቱ ሌላ ተቃውሞ እና አለመረጋገትን ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል።
አዲሱ ፕሬዘዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር እና ተጠባበቂ ፕሬዝዳንት ሳሉ፤ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስሪላካውያን ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በአገሪቱ የተከሰተውን ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ሕዝባዊ አመጽ በርትቶባቸው የነበሩት የቀድሞ የሲሪላንካው ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ በጦር አውሮፕላን ከአገር ከሸሹ በኋላ ሥልጣናቸውን በይፋ መልቀቃቸው ይታወሳል።
ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሲሪላንካውያን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አስተዳደር አካል የሆኑት እና አሁን ፕሬዝዳንት ተብለው የተሾሙት ዊክርሜሲንግህ ለምጣኔ ሃብታዊ ቀውሱ ተጠያቂ ናቸው ይላሉ።
ዊክርሜሲንግህ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው እንደተሾሙ በመላው አገሪቱ የሚጸና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ብዙዎችን ያስቆጣ ነበር።
ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ተላልፈውታል። በወቅቱ ዊክርሜሲንግህ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉትን “ፋሺስቶች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ዊክርሜሲንግህ እራሳቸውን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ አድርገው ከማቅረብ እንዲቆጠቡ ቢጠየቁም ፕሬዝዳንት ሆኖ ከመሾም ያገዳቸው የለም።
አዲሱ ፕሬዝዳንት አገሪቱን ከምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ የማውጣት እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት ቀዳሚው ኃላፊነታቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሲሪላንካ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን የጨረሰች ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟታል። እንደ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና ምግብ የመሳሰሉ መሠረታዊ ቁሶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ተስኗታል።
ሲሪላንካውያን ለዚህ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የአገሪቱን መንግሥት ተጠያቂ ያደርጋሉ። አዲሱ ፕሬዝዳንትም የቀድሞ መንግሥት አስተዳደር አካል ናቸው ይላሉ።
ከፍተኛ ሃብት ካካበቱ ፖለቲከኛ ቤተሰብ የተገኙት ዊክርሜሲንግህ፤ የሕዝብ ተወካዮች አባል የሆኑት ከአራት አስርት ዓመታት በፊት እአአ 1977 ነበር።
ከእአአ 1993 ጀምሮ ዊክርሜሲንግህ በተለያዩ ጊዜያት የሲሪላንካ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።