ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ተጨማሪ የዩክሬንን ግዛት ለመጠቅለል ማቀዷን አሜሪካ አስታወቀች
ሩሲያ ክሪሚያን የጠቀለለችበትን ተመሳሳይ ስልት በመጠቀም ተጨማሪ የዩክሬንን ግዛት የግሏ ለማድረግ ማቀዷን አሜሪካ አስታወቀች።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ኪርቢ፣ የአሜሪካ የስለላ መሥሪያ ቤትን በመጥቀስ ሩሲያ የዩክሬንን ተጨማሪ ግዛት ለመያዝ መሠረት እየጣለች ነው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ሩሲያ ተቆጣጥራ የያዘቻቸውን አካባቢዎች ወደራሷ አካል ለመጠቅለል እስከ መስከረም ድረስ ‘የይስሙላ’ ሕዝበ ውሳኔ ልታደርግ ትችላለች ብለዋል።
ሩሲያ በስፋት ሕገ-ወጥ ተብሎ የሚተች ሕዝበ ውሳኔ አድርጋ ክሪሚያን ከዩክሬን የጠቀለለችው እንደ አውሮፓውያኑ 2014 ነበር።
“ለአሜሪካ ሕዝብ ጉዳዩን ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን። ማንም ሰው በዚህ አይታለልም። [የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን] የ2014 የመጫወቻ ስልታቸውን እየተጠቀሙ ነው” ሲሉ ቃል አቀባዩ ኪርቢ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ሩሲያ ከዩክሬን የያዘቻቸውን ክልሎች ለማስተዳደር ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የሩሲያ ደጋፊ ባለሥልጣናትን ሰይማለች ሲሉም ከሰዋል። ይህም ግዛቶቹን ለመጠቅለል ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
የሕዝበ ውሳኔውን ድምጽ ውጤትም ሩሲያ “የዩክሬንን ሉዓላዊ ግዛት ለመጠቅለል ትጠቀምበታለች” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች የራሷን የግዛት እና የአካባቢ ባለሥልጣናት ሰይማለች።
ክሪሚያ በሩሲያ የተወረረችው እንደ አውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን፣ ሩሲያ ይህን የዩክሬን ግዛት በፍጥነት ሕዝበ ውሳኔ አሰጥታ የራሷ አካል ማድረጓ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሕገ-ወጥ ተደርጎ ነው የሚታየው።
በዚህ ድምጸ ውሳኔ በርካታ የዩክሬን ደጋፊዎች ድምጽ ላለመስጠት አድማ መትተው የነበረ ሲሆን ሕዝበ ውሳኔው ነጻ እና ፍትሐዊ አልነበረም።
በሌሎች የዩክሬን ክፍሎች የሚካሄዱ ሕዝበ ውሳኔዎችም ተመሳሳይ ነው የሚሆኑት። ሩሲያን ለመቀላቀል የሚቃወሙ ተቃዋሚዎችም ይታፈናሉ ተብሏል።
ቃል አቀባይ ኪርቢ፣ "የሩሲያን እቅድ እያጋለጥን ነው ፤ በመሆኑም ዓለም ማንኛውንም ግዛት ለመጠቅለል የተያዘው እቅድ ታስቦ የተደረገ፣ ሕገ ወጥ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ያውቃል” ብለዋል።
ለዚህም ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡም ቃል አቀባዩ ቃል ገብተዋል።
ሩሲያ የግዛቷ አካል ለማድረግ ዒላማ አድርጋቸዋለች ከተባሉ የዩክሬን አካባቢዎች መካከል ክሄርሶን፣ ዛፖሪዝዚያ፣ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ እንደሚገኙበትም ቃል አቀባይ ኪርቢ ተናግረዋል።