ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ወደ ሰሜን ኮሪያ ድሮን በመላካቸው የ30 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ወደ ሰሜን ኮሪያ ድሮን በመላካቸው ተጨማሪ የ30 ዓመት እስራት ፈረደባቸው።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወታደራዊ አገዛዝ ማወጃቸውን ለመሸፈን ፒዮንግያንግን ለማስቆጣት ሞክረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 ወታደራዊ አገዛዝን አውጀው አገራቸውን ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ ከመክተታቸው ጋር በተያያዘ መታሰራቸው ይታወሳል።
ወታደራዊ አገዛዝ ያወጁት አገሪቱን "ከጠላት" ለመከላከል መሆኑን ቢገልጹም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ያቀረቡት የወታደራዊ አገዛዝ ሐሳብ ከከሸፈ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው እንደነበር አይዘነጋም።
የስዑል ቀጣናዊ ዳኛ የቀድሞው ፕሬዝዳንት፣ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ-ሁን፣ የቀድሞው የድሮን ኦፕሬሽን ኃላፊ ኪም ዮንግ-ዴይ እንዲሁም የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ ዮ ኢን-ሁን ሥልጣንን በመበዝበዝ እና አገርን በመክዳት ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
"ተከሳሾቹ በወታደራዊ ኦፕሬሽን ሽፋን ሰሜን ኮሪያን ለመተንኮስ ሞክረዋል። ዓላማቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ነበር" ሲል ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ይፋ አድርጓል።
የቀድሞዎቹ ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያን በመተንኮስ "የወታደራዊ ግጭት ስጋት እንዲባባስ" ማድረጋቸው ተገልጿል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት "ትልቁን ኃላፊነት እንደሚሸከሙም" ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቃ በበኩላቸው ድርጊቱ "ሕጋዊ" እንደሆነ እና ሰሜን ኮሪያ "ቆሻሻ ፊኛዎች በመላክ ለፈጸመችው ትንኮሳ ምላሽ" መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል።
በ2024 ሰሜን ኮሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ በቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳ ይታወሳል።
ከኮሪያ ጦርነት ወዲህ ሁለቱም አገራት አንዳቸው ለሌላቸው "የፕሮፓጋንዳ ፊኛዎች" በመላላክ ይተነኳኮሳሉ።
በ2024 ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያ ድሮን በግዛቷ ማብረሯን መግለጿ ውጥረቱን አባብሶታል።
ድሮኖቹ በፒዮንግያንግ የፕሮፓጋንዳ መልዕክት በትነዋል ስትልም ደቡብ ኮሪያ ከስሳለች። ትንኮሳው ወደ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል አስጠንቅቃም ነበር።
የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ክስ የተመለከቱት ዳኛ እንዳሉት ድሮኖቹ የተላኩት ትንኮሳ በመፈጸም የአጸፋ ምላሽ እንዲሰጥ ለማነሳሳት ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሥልጣናቸውን በመበዝበዝ እና ላለመታሰር በመሞከር የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸውም ነበር።