እስራኤል በቴል አቪቭ ለደረሰው ጥቃት በሁቲዎች ላይ የበቀል እርምጃ ወሰደች

የፎቶው ባለመብት, AP
እስራኤል በቴል አቪቭ የድሮን ጥቃት ከደረሰ ከአንድ ቀን በኋላ በየመን በሁቲ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የቀይ ባሕር ሆዴዳህ ወደብ ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት ለሁቲ መልዕክት ለመላክ ያለመ ጥቃት ነው ብለውታል።
"በሆዴዳ እየነደደ ያለው እሳት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚታይ እና ትርጉሙም ግልጽ ነው" ብለዋል።
የሁቲ ባለስልጣን የሆኑት ሞሐመድ አብዱልሰላም ጥቃቱን “እስራኤል በየመን ላይ የፈጸመችው አረመኔያዊ ጥቃት” ሲሉ ገልጸውታል።
ከሁቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው የዜና አውታሮች በቅዳሜው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ከ80 በላይ ቆስለዋል ብለዋል።
የእስራኤል ጦር እሑድ ጠዋት ከየመን የተተኮሰ ሚሳኤል ወደ እስራኤል የአየር ክልል ከመግባቱ በፊት መምታቱን ተናግሯል።
ስብርባሪው በእስራኤል ኢላት ወደብ “የመውደቅ እድልን ይኖረዋል” በሚል የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ እንዲሰማ መደረጉን አክሏል።
የእስራኤል ጥቃት ሁቲዎች በጋዛ ለፍልስጤማውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያቆሙ ግፊት ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል አብዱልሰላም።
እስራኤል በቅርብ ወራት ውስጥ በግዛቷ ላይ ያነጣጠሩ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የየመን የሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳኤል ጥቃቶች በቀጥታ ምላሽ ስትሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ከፍተኛ የሆነ የእሳት ቃጠሎ እንደነበር ከሆዴዳ የወጡ ምስሎች ያሳያሉ። በሳና የሚገኘውና በሁቲ የሚመራው መንግሥት፤ እስራኤል ከባህር ዳርቻው አቅራቢያ የሚገኝን የነዳጅ ማከማቻን እንዲሁም በአቅራቢያው የሚገኘውን የኃይል ማመንጫ ጣቢያ መታለች ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ “በእስራኤል ላይ ለዘጠኝ ወራት ከዘለቀው የሁቲዎች የአየር ጥቃት በኋላ የእስራኤል አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች በአንድ ሺህ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰፊ ጥቃት አድርሰዋል። ዒላማ የተደረጉትም በሆዴዳ ወደብ አካባቢ የሁቲ አሸባሪ ወታደራዊ ኢላማዎች ናቸው” ብሏል።
“አይዲኤፍ በሚፈለገው ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል እና ማንኛውንም እስራኤላውያንን አደጋ ላይ የሚጥል ኃይልን የመምታት አቅም አለው” ብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው “በምንም መንገድ” እራሷን እንደምትከላከል ከጥቃቱ በኋላ ቅዳሜ ማምሻውን ተናግረዋል።
ወደቡ የኢራን የጦር መሳሪያዎች መግቢያ መሆኑን በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር ገልጸው “በእኛ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሁሉ ዋጋ ይከፍላል" ብለዋል።
እስራኤል ለጠላቶች የማትደርስበት ቦታ አለመኖሩን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።
አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን እንደተናገሩት ኢራን ሰራሽ የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን በመጠቀም አርብ ዕለት በቴል አቪቭ ውስጥ ያሉ አፓርታማዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ሁቲዎች ጥቃቱን እንደፈፀሙት ገልጸው ተጨማሪ ጥቃት ለመፈጸምም ቃል ገብተዋል።
በጥቃቱ በቅርቡ ከቤላሩስ ወደ እስራኤል የሄዱ የ50 ዓመቱን ሰው ገድሎ ስምንት ሰዎችን አቁስሏል።












