የብሪታኒያ አየር መንገድ በአሜሪካ መንግሥት 1.1 ሚሊዮን ዶላር ተቀጣ

ታትሟል

የብሪታኒያ አየር መንገድ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ለተሰረዙ በረራዎች ተመላሽ ገንዘብ ባለመክፈሉ በአሜሪካ መንግሥት 1.1 ሚሊዮን ዶላር ተቀጣ።

የአሜሪካ የትራንስፖርት መሥሪያ ቤት እንዳለው ብሪቲሽ ኤየርዌይስ ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ አሜሪካ እና ከአሜሪካ ወደ ዩኬ ለተሰረዙ አሊያም የበረራ ሰዓታቸው ለተቀየሩ በረራዎች ለመንገደኞች በወቅቱ ገንዘባቸውን አልመለሰም።

በዚህም በአየር መንገዱ ላይ ከ 1 ሺህ 200 በላይ ቅሬታዎች እንደደረሱት ገልጿል።

የብሪታኒያ አየር መንገድ ግን “ በሕግ አግባብ እርምጃ ወስጃለሁ” ሲል ገልጾ፣ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።

እንደ ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቱ ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 2020 መጋቢት እስከ ኅዳር ድረስ የብሪታኒያ አየር መንገድ ደንበኞች ለተሰረዘው አሊያም ለተቀየረው በረራቸው ገንዘባቸው የሚመለስበትን አግባብ በተመለከተ ለመወያየት በስልክ ማነጋገር እንደሚችሉ ለደንበኞቹ በድረ ገፅ አሳውቆ ነበር።

ሆኖም አየር መንገዱ ለደንበኞች አገልግሎት የሚሰጥበት የስልክ መስመር ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ ደንበኞች ለበርካታ ወራት የደንበኞች አገልግሎት ወኪሎችን አግኝተው ማነጋገር አልቻሉም ብሏል።

“በዚህ ወቅትም ደንበኞች በአየር መንገዱ ድረ ገጽ ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የሚጠይቁበት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበረም” ብሏል የትራንስፖርት መሥሪያ ቤቱ።

የትራንስፖርት መሥሪያ ቤቱ ጨምሮም ከመጋቢት እስከ ኅዳር 2020 ድረስ በአየር መንገዱ ድረ ገጽ ላይ የሰፈሩ የተሳሳቱ መረጃዎችም ገንዘባቸው በመመለስ ፋንታ ደንበኞች ተጨማሪ የጉዞ ትኬት እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል ብሏል።

መሥሪያ ቤቱ ከተቀበላቸው ከ 1 ሺህ 200 ቅሬታዎች በተጨማሪ አየር መንገዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅሬታዎች እና ገንዘብ ይመለስልኝ ጥያቄዎች ከደንበኞቹ እንደደረሰውም የትራንስፖርት መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

ለእነዚህ ቅሬታዎች ምላሽ ባለመሰጠቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞች ገንዘባቸው እንዳይመለስላቸው ተግዳሮቶችንና መዘግየትን ፈጥሯል ብሏል።

በመሆኑም ቅጣቱ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳይፈፀም ያደርጋል ብሏል።

ብሪቲሽ ኤየርዌይስ በ2020 እና 2021 የማይመለስ ትኬቶች ላላቸው ደንበኞች ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ ተመላሽ ገንዘብ በመክፈሉ 550 ሺህ ዶላር እዳ ይኖርበታል።

አየር መንገዱ በበኩሉ “ባልተጠበቀው ወረርሽኙ አስጊ ሁኔታ ላይ ባለበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገደናል። መንግሥት በጣለው እገዳ ምክንያት የተወሰኑ የጥሪ ማዕከላትንም ዘግተናል። ደንበኞቻችን የደንበኞች አገልግሎት ቡድን ጋር ለመድረስ ለረዥም ጊዜ እንዲጠብቁ በመደረጋቸውም እናዝናለን።

በዚህ ጊዜም ሁል ጊዜም በሕግ መሠረት እንሰራ ነበር ለደንበኞችም በረራዎቻቸውን ወደ ተለያዩ ቀናት እንዲቀይሩ አሊያም በረራቸው ከተሰረዘም ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው እንዲጠይቁ እድል ሰጥተናል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶም እስካሁን ድረስ ከ5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ገንዘባቸውን ተመላሽ ማደረጉንም አየር መንገዱ ገልጿል።