ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን በሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት 7 ሰዎች ሞተውብኛል፤ 144 ደግሞ ቆስለዋል አለች
የሩሲያ ሚሳዔል በሴሜናዊቷ የዩክሬን ከተማ ባደረሰው ጉዳት አንዲት የስድስት ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ገለጡ።
በቼርኒሂቭ ከተማ ቅዳሜ ጥዋት ደረሰ በተባለው አደጋ 144 ሰዎች መቁሰላችው ሲነገር ከእነዚህ መካከል አስራ አምስቱ ሕፃናት ናቸው ተብሏል።
በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የኦርቶዶክስ ክርስትና በዓል በማክበር ላይ የነበሩ ምዕመናን ይገኙበታል።
አንድ ትልቅ አደባባይ እና የአንድ የዩኒቨርሲቲ ሕንፃም በጥቃቱ መጎዳታቸው ተዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥት ጥቃቱን “ጭካኔ የተሞላበት” ሲለው የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ “ለሽብር ጥቃቱ” የዩክሬን ወታደሮች ከባድ ምላሽ ይሰጣሉ ብለዋል።
ቼርኒሂቭ ከቤላሩስ ድንበር 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ዩክሬንን ሲወሩ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ውላ ነበር።
የከተማዋ ዋና ትያትር በሚሳዔል ጥቃቱ በቀጥታ ሲመታ ከትያትሩ ጣራ ላይ የተበታተኑ ጡቦች እሣት ተፍተዋል።
የከተማዋ ተጠባባቂ ከንቲባ ለቢቢሲ እንደገለጡት ትያትሩ የድሮን አምራቾች ተሰባስበውበት ነበር።
“እኔ እንደገባኝ ዒላማቸው በትያትሩ ግቢ እየተካሄደ የነበረው ወታደራዊ ትዕይንት ነው” ብለዋል ኦሌክሳንደር ሎማኮ።
የዩክሬን ሃገር ውስጥ ሚኒስትር ኢሆር ክላይሜንኮ በትያትሩ የነበሩ ሰዎች ከጥቃቱ በፊት ከለላ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አክለው “ብዙዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ጥቃቱ ሲደርስ በመኪና እና በእግር መንገድ ሲያቋርጡ የነበሩና ከቤተ-ክርስትያን ሲመለሱ የነበሩ ናቸው” ብለዋል።
የቼርኒሂቭ ማዕከል በተለይ ቅዳሜና እሑድ በርካቶች የሚያዘወትሩት ሥፍራ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከትያትሩ ተሻግሮ የሚገኝ አንድ የምግብ ቤት ባለቤት የሆነችው አና ሠራተኞች ለመስተንግዶ ደፋ ቀና እያሉ ሳለ ነው ጥቃቱ የደረሰው ብላለች።
“ፍንዳታውን ሰምቼ ወደ ውጭ ስወጣ ሁለት የ12 ዓመት ሕፃናት ደም በደም ሆነው መንገድ ላይ ወድቀዋል። አንደኛዋ እየጮኸች ነበር፤ ሌላኛዋ ደግሞ እግሯ ቆስሏል” ትላለች።
ቅዳሜ ማታ በቪድዮ መግለጫ የሰጡት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሩሲያ ጥቃት የተገደለችው ሕፃን ስሟ ሶፊያ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሐዘን ታውጇል።
ስለጥቃቱ ሞስኮው እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።
በተያያዘ ዜና የዩክሬን ድሮን በኖቭጎሮድ ከተማ ያለ አንድ ወታደራዊ አየር ማረፊያን መትቶ እሣት መነሳቱን ሩሲያ ገልጣለች።
አክላ በጥቃቱ አንድ አውሮፕላን ጉዳት ቢደርስበትም በሰዎች ላይ ግን ምንም ጉዳት አልደረሰም ብላለች።
የኪይቭ አየር ኃይል ደግሞ ከሞስኮው ከተተኮሱ 17 ኢራን ሠራሽ ሳሔድ ድሮኖች መካከል 15ቱን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።