እስራኤል በራፋህ የምታደርገውን ወረራ አጠናክራ ተጨማሪ ነዋሪዎች ከከተማው እንዲወጡ አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ወረራዋን ማጠናከሯን ተከትሎ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ፍልስጤማውያን ራፋህን ለቀው እንዲወጡ አስጠነቀቀች።
በራፋህ የተበተኑ በራሪ ወረቀቶችና የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች ነዋሪዎች ከምሥራቃዊ አካባቢ ወጥተው ወደ አል-ማዋሲ እንዲሄዱ ያስጠነቅቃሉ።
በራፋህ ነዋሪዎችን በተፈናቃዮች ተጨናንቀው የነበሩ የከተማዋ አካባቢዎች አሁን ሕይወት አልባ ሆነዋል።
አሜሪካና ሌሎችም የእስራኤል አጋሮች በራፋህ ወረራ እንዳይቀጥል ማሳሰቢያ ቢሰጡም እስራኤል በዕቅዷ መሠረት እንደምትቀጥል ገልጻለች።
በራፋህ የሚደረግ ወረራ በርካታ ንጹኃንን ለሞትና ጉዳት እንደሚዳርግ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዳሉት ሐማስ ታጋቾችን ከለቀቀ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ ቀላል ነው።
“እስራኤል ውሳኔው የሐማስ ነው ብላለች። ታጋቾቹን ከለቀቁ በነጋታው የተኩስ አቁም ይደረጋል” ብለዋል።
ሐማስ አግቶ ከወሰዳቸው 128 ሰዎች መካከል 36ቱ እንደሞቱ ይገመታል።
ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ ከራፋህ ወደ ግብፅ በሚያሻግረው አካባቢ የአየር ድብደባ ተፈፅሟል ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ በኤክስ ገፁ ላይ እንዳለው፣ ባለፉት ቀናት በራፋህ የእስራኤል ወታደሮች ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር “ፊት ለፊት ውጊያ ገጥመዋል”።
ከመሬት በታች ብዙ ምሽጎች እንዳገኙም ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት በርካታ የአየር ጥቃቶች በጋዛ ሰርጥ ላይ ተሰንዝረዋል። እስራኤል ዒላማው አሸባሪዎችና የአሸባሪዎች መሠረተ ልማት ነው ትላለች።
ወታደሮቿ ከዚህ ቀደም ጥለውት ወደወጡት ሰሜናዊ ጋዛ ተመልሰው ስለሚገቡ ነዋሪዎች እንዲወጡም ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።
መከላከያው እንዳለው በሰሜናዊ ጋዛ በምትገኘው ጃባሊያ ውስጥና በአቅራቢያዋ የሚገኙ ነዋሪዎች በምዕራብ ጋዛ ወደሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ መሄድ አለባቸው።
ይሄም “የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ነው” ብሏል።
ከዚህ ቀደም ከጃባሊያ የተፈናቀሉ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በስልካቸው የደረሳቸው መልዕክት በአፋጣኝ ለቀው እንዲወጡ ያሳስባል።
“የት እንደምንሄድ አናውቅም። ወደ 80 የምንደርስ ሰዎች ነን። ወደ ካሃን ዩኑስ የምመለስበት ገንዘብ የለኝም። ጎረቤቶቼ እዛ ሄጄ በርካሽ ቤት እንድከራይ መክረውኛል። ግን ወደዛ የሚወስደኝ መኪና የምከራይበት ገንዘብ የለኝም።”












