ናታንያሁ፣ አሜሪካ የጦር መሣሪያ መላክ ብታቆም እንኳ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ዛቱ

ቤኒያሚን ናታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, "ብቻችንን እንኳ ብንሆን ጸንተን እንቆማለን" ናታንያሁ
ታትሟል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ እስራኤል ‘ብቻዋን ፀንታ ትቆማለች’ አሉ።

ይህን ያሉት አሜሪካ የጦር መሣሪያ ለእስራኤል የመላኩን ጉዳይ አጤነዋለሁ ስትል መዛቷን ተከትሎ ነው።

አሜሪካ ይህን አቋም ለመውሰድ እየተገደደች ያለችው ናታንያሁ በጋዛ ራፋህ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳይከፍቱ ከባይደን የተላከላቸውን መልእክት ቸል በማለታቸው ነው።

“ብቻችንን መቆም ካለብን ያን እናደርጋለን፤ አስፈላጊ ከሆነ በጨበጣም ቢሆን እንዋጋለን” ሲሉ ዝተዋል፣ ናታንያሁ።

ባይደን በበኩላቸው ራፋህ ላይ እስራኤል ወረራ ከፈጸመች የተወሰኑ ጦር መሣሪያዎችን መላክ እናቆማለን ብለዋል።

አሜሪካ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን እልቂት ተከትሎ የተወሰኑ ቦምቦችን ወደ እስራኤል መላክ አቁማለች።

ናታንያሁ ሐሙስ ዕለት ባደረጉት ንግግር እስራኤል የተመሠረተችበትን 1948 ዓመተ ምሕረት አንስተው አሁን ገጠመን ካሉት መገለል ጋር አዛምደውት ነበር።

“የዛሬ 76 ዓመት ነጻ ለመውጣት ስንዋጋ ብቻችንን ነበርን። ጦር መሣሪያ አልነበረንም። ማዕቀብ ተጥሎብን ነበር። ነገር ግን በታላቅ ጀብድ እና ጥንካሬ ድል አድርገን ወጣን።”

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላን በበኩላቸው፣ “ለወዳጅም ለጠላትም መናገር የምንሻው እስራኤልን ማንም ማንበርከክ እንደማይችል ነው። ግባችንን ከመምታት የሚያቆመን አንዳችም ኃይል የለም” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በራፋህ ጥቃትን በመፍራት ከሰኞ ወዲህ ብቻ 80ሺህ ሰዎች ለቀዋል። እስራኤል በራፋህ ጥቃት ከፍታለች።

የተባበሩት መንግሥታት በራፋህ ጥቃት ከተሰነዘረ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንደሚፈጠር አስጠንቅቋል። ምግብና ነዳጅ እጥረት መከሰት መጀመሩንና ከተማዋ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ፍልስጤማዊያን መፈናፈኛ ሊያጡ እንደሚችሉ ተናግሯል።

የእስራኤል ወታደሮች ራፋህና ግብጽን የሚያገናኘውን መስመር ተቆጣጥረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ይህ መስመር መያዙ ለሠራተኞቹና ለእርዳታ አቅራቢዎች አደገኛ እንደሆነ ገልጧል።

እስራኤል እንደምትለው በራፋህ የሐማስ ርዝራዥ ስለሚገኝ እሱን የማጽዳት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ባይደን ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ለሲኤንኤን ቴሌቪዥን እንደተናገሩት “አሜሪካ ሠራሽ ቦምቦች በጋዛ ሰላማዊ ዜጎችን ለመግደል አገልግሎት ላይ ውለዋል። እስራኤል ወደ ራፋህ ወረራ ከፈጸመች ግን እነዚህ ቦምቦች አል’ልክም” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐማስና እስራኤል እያደረጉ ያሉት ድርድር ጫፍ ከደረሰ በኋላ አልሰመረም።

የእስራኤልና የሐማስ ተደራዳሪዎች ትናንት ካይሮን ለቀው መውጣታቸው ተሰምቷል።

በጋዛ ላለፉት ሰባት ወራት እስራኤል በፈጸመችው ወረራ ከ34ሺህ ፍልስጤማዊያን በላይ ተገድለዋል። ከነዚህ የሚበዙት ደግሞ ሕጻናትና ሴቶች ናቸው ብሏል፣ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር።