በስፔን ዩክሬናውያን ይበዘበዙበታል የተባሉ በወሮበሎች የሚመሩት ሦስት የትምባሆ ፋብሪካዎች ተገኙ

ታትሟል

የስፔን ፖሊስ ሦስት ሕገ ወጥ የትምባሆ ፋብሪካዎችን ይመራል ያለውን የወሮበሎች ቡድንን ባደረገው ዘመቻ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ።

እነዚህ የትንባሆ ማምረቻዎች ሕገ ወጥ ከመሆናቸው በተጨማሪ የዩክሬን ዜግነት ያላቸው ስደተኞችን ለሥራ በማይመች ሁኔታ ውስጥ በማሰራት ይበዘበዙ ነበር ተብሏል።

ዘመቻው በስፔን ሦስት ግዛቶች ውስጥ የተከናወነ ሲሆን 27 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

የወሮበላ ቡድኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ትምባሆ በሲጋራ መልክ በማዘጋጀት ያዘዋውር ነበር ተብሏል።

ፋብሪካዎቹ በስፔን እና በሌሎች አገራት የሚሽጡ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ እሽግ ሲጋራዎችን በቀን ያመርቱ ነበር።

የሩሲያን ወረራ በመሸሽ የተሰደዱ ዩክሬናውያን በፋብሪካዎቹ ውስጥ ባሉ መጠለያዎች ተጨናንቀው ይኖሩ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

ዩክሬናውያኑ ለረጅም ሰዓታት እንደሚሰሩ እና አንዳንዶቹ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ በመሆናቸወን ጥርጣሬን ለማስወገድ ከፋብሪካዎቹ መውጣት አይፈቀድላቸውም።

ይህ ሲሆን የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች ቅንጡ ሕይወትን የሚመሩ እና ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ሕጋዊ በማስመሰል ለትምባሆ ምርት ያውላሉ ተብሏል።

በዘመቻውም 41 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የትንምሆ ምርት፣ ቅንጡ ተሽከርካሪዎች፣ ጌጣ ጌጦች እና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተገኝቷል።

ይህ ዘመቻ ሲካሄድ ከ20 በላይ ቤቶች፣ የኢንዱሰትሪ ህንጻዎች እና ሱቆች ላይ ፍተሻ ተካሂዷል።

የመጀመሪያው በድብቅ ሲካሄዱ የነበሩት ሕገ ወጥ የትምባሆ ፋብሪካ በስፔን ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ የዶሮ እርባታ ቦታ የተገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፤ ከዚያ በኋላም ሁለት ፋብሪካዎች ደግሞ በአገሪቱ ምሥራቃዊ እና ሰሜናዊ ክፍል ተገኝተዋል።

እነዚህን ፋብሪካዎች የሚያንቀሳቅሰው የወንጀለኞች ቡድን በማሪዋና ምርት ላይ በመሰማራት ሕገወጥ ተግባራትን ሲያስፋፋ ነበር ሲል ፖሊስ ገልጿል።

የስፔን ፖሊስ በዚህ የወንጀል ድርጊት ላይ ባደረገው ምርመራ ውስጥ የአውሮፓ ፖሊስ አካል ዩሮፖል እገዛ አድርጓል።

ሩሲያ ባለፈው ዓመት ዩክሬን ላይ የፈጸመችን ወረራ በመሸሽ ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ የተመዘገቡ ዩክሬናውያን ስድተኞች በመላው አውሮፓ እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ የሳያል።

ከእነዚህም መካከል ከ160 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስፔን ውስጥ ይገኛሉ።

ባለፈው ጥቅም ላይ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ዩክሬናውያን በሥራ ላይ የሚበዘበዙበት መጠን እየጨመረ መሆኑን ገልጿል።

ዩክሬናውያን ስደተኞች ባለባቸው የቋንቋ ችግር ምክንያት መደበኛ ያልሆነ እና ዝቅተኛ ክፍያ ባላቸው ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ አስገድዷቸዋል ተብሏል።

የአህጉሪቱ ፓርላማም ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ ምላሽ እንደሚፈያስፈለገው አሳስቧል።