የደቡብ ሱዳን የውሃ ሚኒስትር ግብፅ ውስጥ ሕይወታቸው አለፈ

የደቡብ ሱዳን ውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትር ማናዋ ፒተር ጋትኩት ጉአል

የፎቶው ባለመብት, SPLM / IO

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ሱዳን ውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትር ማናዋ ፒተር ጋትኩት ጉአል
ታትሟል

የደቡብ ሱዳን ውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትር ማናዋ ፒተር ጋትኩት ጉአል በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን የአገራቸው መንግሥት አስታወቀ። 

ሚኒስትሩ በደረታቸው አካባቢ የነበረው ህመም ጸንቶባቸው ባለፈው አርብ ወደ ግብፅ ለህክምና ተጉዘው እንደነበር የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ገልጸዋል።

የታመሙት የውሃ ሚኒስትር ግብፅ ከደረሱ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ቀዶ ሕክምና የተረገላቸው ቢሆነም የዚያኑ ዕለት ማምሻውን ሕይወታቸው ማለፉን ነው ሪክ ማቻር የተናገሩት።

“ማናዋ በዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ጊዜ ጠንካራ የተማሪዎች መሪ ነበሩ። በሱዳንም የወጣቶች ንቅናቄ ላይ ጥሩ መሪ ነበሩ። ቆራጥ እና አገራዊ ፍቅር ያላቸው ነበሩ። በደቡብ ሱዳን ላይ ጠንካራ እምነት የነበራቸውም ሰው ነበሩ” ብለዋል ማቻር ለቤተቦቻቸው ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳለቫ ኪር በበኩላቸው የውሃ ሚኒስትሩን ሞት ሲሰሙ “ታላቅ ሐዘን” እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የደቡብ ሱዳን ውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትር ማናዋ ከመንግሥታዊ ሥልጣናቸው ባሻገር የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ [ኤስፒኤልኤም - አይኦ] የተባለው ቡድን የፖለተካ ዘርፍ አባልም ነበሩ።

የሚኒስትሩ አባት ፒተር ጋትኩት ጉአል በደቡብ ሱዳን ሰፊ እውቅና ያላቸው ፖለቲከኛ ነበሩ።