ኤቨርተን ሲተርፍ ሌስተርና ሊድስ ወርደዋል፤ ሲቲ ተሸንፎ አርሰናል በሰፊ ጎል የውድድር ዘመኑን አጠናቋል

አብዱላይ ዱኩሬ ጎሏን ካስቆጠረ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የእንሊግዝ ፕሪሚዬር ሊግ እሑድ ምሽት ተገባዷል። ኤቨርተን፤ ሊድስና ሌስተርን ገፍትሮ ከመውረድ ተርፏል።

በመጨረሻው የሊጉ መርሐ ግብር ከሁሉም ጨዋታዎች አጓጊ የነበረው የትኞቹ ቡድኖች ይወርዳሉ የሚለው ነበር።

አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ሳውዝአምፕተን ከሊቨርፑል አስደናቂ ፍልሚያ አድርጎ 4-4 ተለያያይቷል።

ሌሎች የመውረድ ስጋት አሊያም የመቆየት ተስፋ የነበራቸው ቡድኖች ኤቨርተን፣ ሌስተርና ሊድስ ነበሩ።

ከሶስቱ ቡድኖች ላለመውረድ የተሻለ ዕድል የነበረው ኤቨርተን በጉዲሰን ፓርክ ከቦርንመዝ የነበረውን ግጥሚያ በድል መውጣት ነበረበት።

ሊድስ ከቶተንሃም፤ ሌስተር ደግሞ ከዌስትሃም ያደረጉት ጨዋታም የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር።

ከአርሰናል ቀጥሎ በሊጉ ለበርካታ ዓመታት የተጫወተው ኤቨርተን በአብዱላየ ዱኩሬ ጎል አስጨናቂውን ጨዋታ በድል ተወጥቷል።

ኤቨርተን በእንግሊዝ ከፍተኛ ሊግ ለ69 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን ከዱኩሬ ጎል በፊት ግን ይህ 70ኛ ዓመት ይደፍኑ ይሆን የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ተገኝቷል።

ኤቨርተን ከቦርንመዝ ያለምንም ጎል ሳለ፤ ሌስተር በሜዳው ዌስትሃምን መምራት መጀመሩ የጉዲሰን ፓርክ ተመልካቾችን አስጨንቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዱኩሬ ጎሏን ሲያስቆጥር ጉዲሰን ፓርክ በርችት አሸበረቀ። ደጋፊዎች መቆሚያ መቀመጫ አጡ።

ቢሆንም ጨዋታው በኤቨርተን አንድ ለምንም ጎል መቀጠሉ፤ ሌስተር ደግሞ ዌስትሃምን 2-1 መምራቱ ሌላ ጭንቀት ሆነ።

90ኛው ደቂቃ ሲደርስ አራተኛው ዳኛ ተጨማሪ ደቂቃ ማሳያቸው ላይ ሌላ ጭንቀት አዝለው ከች አሉ። 10 ደቂቃ።

ጨዋታቸውን በድል ያጠናቀቁት ሌስተሮች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሜዳው መሃል ቁጭ ብለው የኤቨርተን ጨዋታ ማየት ጀመሩ።

በስተመጨረሻም 100 ደቂቃ የተፋለመው ኤቨርተን ጨዋታውን በድል ሲወጣ ሌስተርና በቶተንሃም 4-1 የተሸነፈው ሊድስ ወደታችኛው ሊግ መውረዳቸው እርግጥ ሆነ።

በሌሎች ጨዋታዎች ቻምፒዮኖቹ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ብሬንትፈርድ አቅንተው 1-0 ተረትተዋል።

የዋንጫ ተፎካካሪ የነበሩት አርሰናሎች ደግሞ በኤሜሬትስ ዎልቭስን 5 ለምንም ረምርመዋል።

ምናልባት በአርሰናል ቤት የመጨረሻው ጨዋታ ሊሆን ይችላል የተባለለት ዣካ ሁለት ጎሎ ሲያስቆጥር፤ ሳካ እና ጋብርኤል እንዲሁም ተከላካዩ ኪዊዮር የአርሰናልን ጎሎች አስቆጥረዋል።

አስተን ቪላ በሜዳው ብራይተንን በመርታት ከ13 ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ እግር ኳስ ተመልሷል።

በዳግላስ ሉዊዝ እና ዋትኪንስ ጎሎች ታግዞ ድል የተጎናፀፈው ቪላ፤ ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ይጫወታል።

በሌሎች ጨዋታዎች ቼልሲ ከኒውካስል፤ እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ አንድ አቻ ጨርሰዋል።

ቶተንሃም ከሜዳው ውጭ ሊድስ ዩናይትድ 4-1 ቢረታም ስምንተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ በአውሮፓ ውድድሮች በቀጣይ የውድድር ዘመን አይታይም።

ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በኦልድ ትራፈርድ ፉልሃምን አስተናግዶ ድል ተቀዳጅቷል።

በ19ኛው ደቂቃ በቴቴ ጎል መሪነቱን የወሰዱት ፉልሃም ከ7 ደቂቃ በኋላ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ዴቪድ ዴ ሂያ የሚትሮቪችን ኳስ አድኗል።

ዩናይትድ በመጀመሪያው አጋማሽ በሳንቾ፤ በሁለተኛው አጋማሽ በፈረናንዴዝ አማካይነት ባስቆጠራቸው ጎሎች አሸንፏል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች 15ቱን በድል ጨርሷል።

ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች ዩናይትድ ከሲቲ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ይገናኛሉ።