ኢራን የታዋቂው እግር ኳስ ተጫዋች ቤተሰብ ከአገር እንዳይወጡ አደረገች

ኢራናዊው ስመ ጥር የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች አሊ ዴኢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ኢራናዊው ስመ ጥር የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች አሊ ዴኢ ባለቤቱ እና ሴት ልጅ ሃገሪቱን ለቀው እንዳይወጡ ለማድረግ ዓለም አቀፍ በረራ አቅጣጫ እንዲቀይር መደረጉን ተናገረ።

የ53 ዓመቱ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች እንዳለው ቤተሰቡ በዓሉን አብረው ለማክበር ከቴህራን ተነስተው እሱ ወደሚኖርበት ዱባይ ለመጓዝ በአውሮፕላን ተሳፍረው ነበር።

ሆኖም በረራው ከጀመረ በኋላ አውሮፕላኑ አቅጣጫውን እንዲቀይር ተደርጎ በአንድ ደሴት ላይ እንዲያርፍና ቤተሰቦቹ እንዲወርዱ ተደርገዋል ብሏል።

ለዚህ ምንም አይነት ምክንያት ያልተሰጠው ሲሆን ወደ ቴህራንም እየተመለሱ ነው ሲል አሊ አክሏል።

አሊ በኢራን መንግሥት ላይ ለተነሳው ተቃውሞ ድጋፉን በመስጠትም ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት አገሪቷን እያናወጣት ያለው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የ22 አመቷ ኢራናዊት ማህሳ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች መሞቷን ተከትሎ ነው። ግለሰቧ በእስር ላይ የዋለችው የሂጃብ ህጉን ተላልፋ ጸጉሯን በትክክል ባለመሸፈን ነው።

ከነዚህ ተከታታይ ተቃውሞዎች ጋር ተያይዞም 69 ህጻናትን ጨምሮ ከ500 በላይ ተቃዋሚዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መታሰራቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ገልጸዋል። በርካታ የኢራን የደህንነት አባላት መገደላቸውም ተዘግቧል።

የኢራን መንግሥታዊ የዜና ወኪል ኢርና በበኩሉ የአሊ ባለቤት ሞና ፋሮካዛሪ ሃገሪቷን ለቃ ከመውጣቷ በፊት ባለስልጣናቱን ለማሳወቅ ቃል ገብታ ነበር ብለዋል። ይህም ጥንዶቹ “በእስልምና አብዮት ተጻራሪ ከሆኑ ቡድኖች” ጋር ግንኙነት ስላላቸውም ነው ብሏል ዘገባው።

ኢርና አውሮፕላኑ ኪሽ ደሴት ላይ አርፎ የአሊ ባለቤትና ልጅም እንዲወርዱ መደረጉንም ዘግቧል።

ባለቤቱና ልጆቹ ዱባይ ለጥቂት ቀናት ለመቆየትም አቅደው እንደነበር የተናገረው አሊ በበኩሉ “ከአገር መውጣት ተከልክለው ከሆነ የፓስፖርት ተቆጣጣሪ ስርዓቱ ማሳየት ነበረበት። ያሳወቀኝም የለም” ብሏል።

ተጫዋቹ በመስከረም ላይ በማህበራዊ ገጹ ባጋራው ጹሁፍ መንግሥት "ጭቆና፣ ጥቃት እና እስራት ከመጠቀም ይልቅ የኢራንን ህዝብ ችግር እንዲፈታ" አሳስቦ ነበር።

ከዚህ ቀደም ብሎም ቴህራን የሚገኘው የጌጣጌጥ ሱቁ እና ሬስቶራንቱ በፍትህ አካላት ተዘግቷል።

ከታሰሩት በተጨማሪ ህዝባዊ ተቃውሞውን የደገፉ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች ከሀገር እንዳይወጡ በአገሪቱ ባለስልጣናት ተከልክለዋል።

የ53 አመቱ አሊ ዴኢ በኢራን ታዋቂ ከሆኑ የስፖርት ሰዎች አንዱ ነው።

የኢራን ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድንን  በአምበልነት የመራ ሲሆን በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ 109 ጎሎችን አስቆጥሯል።