ፍቅረኛውን የገደለው ኦስካር ፒስቶሪየስ ከዓመታት እሥር በኋላ በአመክሮ ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፓራሊምፒክስ ተወዳዳሪ የነበረው ደቡብ አፍሪካዊው ኦስካር ፒስቶሪየስ ፍቅረኛው ሪቫ ስቲንካምፕ ከገደለ ከ11 ዓመታት በኋላ በአመክሮ ተለቀቀ።
ባለሥልጣናት እንደገለጡት ኦስካር 13 ዓመት ተፈርዶበት ከግማሽ በላይ እሥር ቤት ከቆየ በኋላ አርብ ንጋት “ቤት ተመልሷል።”
የስቲንካምፕ እናት ገዳዩ ኦስካር መለቀቁ ቅር ባያሰኛቸውም “ዕድሜ ልክ ቅጣት የተቀጣው ግን ቤተሰባችን ነው” ብለዋል።
አሁን 37 ዓመት የሞላው ኦስካር በአውሮፓውያኑ 2013 ነበር ፍቅረኛውን ከበር ጀርባ በሽጉጥ ደጋግሞ መትቶ የገደላት።
ሁለት እግር የሌለው ኦስካር ምርመራ ሲደረግበት ዘራፊ መስሎት በሽጉጥ እንደገደላት ገልጧል።
ኦስካር በአውሮፓውያኑ 2015 በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ፍርድ ቤት በእሥር እንደቀጣው ይታወሳል።
በደቡብ አፍሪካ ሕግ መሠረት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ወንጀለኞች በአመክሮ ለመለቀቅ ጥያቄ የማቅረብ መብት አላቸው።
ጥፋተኞች አብዛኛውን ጊዜ ከተፈረደባቸው ጊዜ ግማሹን ካገለገሉ በኋላ በአመክሮ ሊለቀቁ ይችላሉ።
ኦስካር ፒስቶሪየስም ከተፈረደበት 13 ዓመት መካከል ከግማሽ በላይ እሥር ቤት ከርሞ ቢወጣም የቀረውን ጊዜ በጥብቅ ሕግና በተወሰነ መብት መንቀሳቀስ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ መሠረት ለተወሰኑ ሰዓታት ከቤት መውጣት አይችልም አልፎም አልኮል መጠጣት አይፈቀድለትም። ለሚድያ ቃሉን መስጠትም ሕግ አይፈቅድለትም።
ከዚህ በተጨማሪ ፆታዊ ጥቃት እና ንዴትን ለማስታገስ የባለሙያ ምክር ማግኘት ይኖርበታል።
ኦሰካር ከእሥር ቤት ከወጣ በኋላ በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ በሚገኘው የአጎቱ መኖሪያ ቤት እንዳረፈ ተሰምቷል።
አትሌቱ እሥር ቤት ሳለ የማረሚያ ቤቱን ቅጥር ግቢ አረም በማሽን በመንቀል፣ ቤተ-መፃሕፍት በመሥራት እና የታራሚዎችን መፀዳጃ ቤት በማፅዳት አገልግሏል።
የማሕበረሰብ አገለግሎት ሰጪዎችና የሥነ-ልቡና ባለሙያዎች ኦስካር የፀባይ ለውጥ እንዳሳየ መስክረዋል።
የሟች እናት ጁን ስቲንካምፕ ኦስካር በአመክሮ ከእሥር ቤት ሊለቀቅ እንደሚችል ቤተሰቡ እንደሚያውቅ ተናግረዋል።
እናት “ምንም ቢሆን ልጃችን ተመልሳ እስካልመጣች ድረስ ፍትሕ ሰፍኗል ብለን አናስብም” ሲሉ ኦስካር ፍርዱን ቢያገለግልም ልጃቸውን መልሰው ማግኘት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ኦስካር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሥር ቤት ያቀናው በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2014 ነበር። በ2015 አና 2016 መካከል ለተወሰነ ጊዜ ከእሥር ቤት ተለቆ በቁም እሥር ቆይቶ ነበር።
ኦስካር ሁለት እግሮቹን ያጣው ገና አንደኛ ዓመቱን ሳይደፍን ነበር። ነገር ግን ይህ ሳይበግረው በተቀጠለለት እግር ተጠቅሞ ውጤታማ አትሌት መሆን ችሏል።
በአትሌትነትን ዘመኑ በጣም እውቅና አግኝቶ “ዘ ብሌድ ራነር” የተሰኘ ስም አትርፎ ነበር።
ፒስቶሪየስ በፓራሊምፒክ ውድድር በርካታ ሜዳሊያዎች ከሰበሰበ በኋላ በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ተፈጥሯዊ እግር ካላቸው ሯጮች ጋር ተወዳድሯል።
ከስድስት ወራት በኋላ ፍቅረኛውን መግደሉ ተሰምቶ የዓለም መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
ፍቅረኛው ሪቫ ስትገደል 29 ዓመቷ ነበር። የሕግ ምሩቅ የነበረችው ሪቫ ውጤታማ ሞዴል እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂም ነበረች።












