በአሜሪካ አንድ ውሻ ቤት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ 4 ሺህ ዶላር ቅርጥፍ አድርጎ በላ

የፎቶው ባለመብት, CLAYTON AND CARRIE LAW
ገንዘብ የተራበ አንድ ውሻ ባለቤቶቹ ቤት ውስጥ ያስቀመጡትን 4 ሺህ ዶላር ቅርጥፍ አድርጎ በላ።
ሴሲል የተባለው ውሻ ባለቤቶቹ ለኮንትራክተር ለመክፈል በፖስታ ያስቀመጡትን ገንዘብ ነው የበላው።
ክሌይተን እና ካሪ ሎው የተባሉት የሴሲል ባለቤቶች፤ ውሻቸው የበጫጨቀውን እና ውጦ ያስመለሰውን ዶላር ሰብስበው አጣብቀዋል። እንደዚህም ሆኖ 450 ዶላር አሁንም ጠፍቷል ተብሏል።
ሴሲል ዶላር መብላቱ በጤናው ላይ አደጋ እንደማያመጣ የእንስሳት ሐኪሙ ለጥንዶቹ ነገረዋቸዋል።
በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ክሌይተን ሎው በፒትስበርግ ፔንስልቬንያ በሚገኘው መኖሪያ ቤት መደርደሪያ ላይ 4 ሺህ ዶላር የያዘ ፖስታ ያስቀምጣል። ይህ ገንዘብ አጥር ለሠራላቸው ኮንትራክተር በጥሬ ለመክፈል ያዘጋጁት ገንዘብ ነው።
ከ30 ደቂቃ በኋላ ክሌይተን ውሻው በሕይወቱ እጅግ ውድ የሆነ ምግብ ሲመገብ አገኘው። ገንዘቡን ከመብላት ባለፈ በየቦታው የተበታተኑ የዶላር ቁርጥራጦችን አገኘ።

የፎቶው ባለመብት, Clayton and Carrie Law
ካሪ ሎው ከፒትስበርግ ሲቲ ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ላይ "በድንገት ክሌተን ‘ሲሲል 4 ሺህ ዶላሩን እየበላ ነው!’ ብሎ ጮኸ። ይህን መስማት አልችልም ብዬ አሰብኩ። የልብ ድካም የሚገጥመን መስሎኝ ነበር።"
"እሱ በጣም ልዩ ፍጥረት ነው። በጠረጴዛው ላይ ስጋ ትተህ መሄድ ትችላለህ። የእሱ ምግብ ስላልሆነ አይነካውም። በግልጽ ግን ለገንዘብ ልዩ ፍላጎት ነበረው” ስትል ካሪ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግራለች።
ጥንዶቹ ውሻው ህክምና የሚያስፈልገው እንደሆነ ለማወቅ ወዲያውኑ ወደ የእንስሳት ሐኪም ደወሉ። እንደ ዕድል ሆኖ ሴሲል ትልቅ ውሻ በመሆኑ በቤት ውስጥ ብቻ ክትትል ማደረግ እንዳለባቸው ተነገራቸው።
ከዚያም ጥንዶቹ ያልተጠበቀው እና አድካሚውን የተቆራረጡ ገንዘቦችን የማጣበቅ ሥራ ጀመሩ።
ገንዘቡን አንድ ላይ ማጣበቅ ከመጀመራቸው በፊት ሴሲል ገንዘቡን እስኪያስመስለው ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ቀጥለውም ዶላሩን በደንብ አጸዱት።
“የዕቃ ማጠቢያ ገንዳ ውስጥ ነበር። በጣም መጥፎ ሽታ ነበረው" ብላለች ካሪ።

የፎቶው ባለመብት, CLAYTON AND CARRIE LAW
ቀጥሎም ጥንዶቹ የተበላሹትን ባለ 50 እና ባለ 100 ዶላር ኖቶችን አንድ በአንድ ለማጣበቅ ሞከሩ። ባንክ እንዲቀበላቸው እና በአዲስ የገንዘብ ኖት እንዲተካላቸው ለማድረግ ዶላሩን በሁለቱም በኩል ተመሳሳይ መሆኑን እያረጋገጡ አጣብቀዋል።
ባንኩ አብዛኛዎቹን ገንዘቦች ተቀብሏቸዋል። የከሰሩት 450 ዶላር ብቻ ነው። የባንክ ባለሙያዎች እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች በጣም የተለመዱ መሆናቸውን ለጥንዶቹ ነገረዋቸዋል።
ጥንዶቹ "የቀሩት ቁርጥራጭ ዶላሮች በጣም ውዱ የጥበብ ስራችን ይሆናሉ" ሲሉ ጽፈዋል።
በ2022 ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል ሲል ኒውስዊክ ዘግቧል። አንዲት በፍሎሪዳ ያለ ውሻ 2 ሺህ ዶላር በልቷል። በወቅቱ ውሻውን በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ባደረገው ቪዲዮ የቤት እንስሳውን ባለቤት ስታለቅስ ታይቷል።












