በናይጄሪያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጠመንጃ ታጥቀው የሰበኩት ፓስተር መነጋገሪያ ሆኑ

ፓስተር ኡቼ አይግቤ ጠመንጃ ታጥቀው በስብከት ላይ

የፎቶው ባለመብት, HOUSE ON THE ROCK CHURCH

የምስሉ መግለጫ, ፓስተር ኡቼ አይግቤ ጠመንጃ ታጥቀው በስብከት ላይ
ታትሟል

ናይጄሪያዊው ፓስተር እሁድ ዕለት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ታጥቀው ስበከት ላይ መገኘታቸው በምዕመናኑ ዘንድ ግራ መጋባትን ሲፈጥሩ በአገሪቱ ውስጥ መነጋገሪያ ሆነዋል።

በአቡጃ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ‘ሐውስ ኦን ዘ ሮክ’ የተባለው ቤተከርስቲያን ሰባኪ የሆኑት ኡቼ አይግቤ፣ ትናንት እሁድ ለስበከት ወደ መድረክ የወጡት ኤኬ47 የተባለው ጠመንጃ አንግበው ነበር።

በርካታ ምዕመን በታደመበት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ፓስተሩ ጠመንጃ ታጥቀው ወደ መድረኩ ሲወጡ በርካቶች ግራ ተጋብተው የነበረ ሲሆን፣ ይህንን የሚያሳየው ቪዲዮም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ታይቷል።

ፓስተሩ በትምህርታቸው ወቅት ጠመንጃ መታጠቃቸውን የምእመናኑን “ልብ ከሐሰተኛ መምህራን ከመጠበቅ” እና “እምነት ያለ ሥራ ምንም መሆኑን” ለማሳየት ተጠቅመውበታል ተብሏል።

ፓስተሩ ሐሰተኛ መምህራን ያሏቸውን በተመለከተ ድርጊታቸውን በስፋት ያብራሩ ሲሆን፣ “ስለዚህም የእምነት መሳሪያችንን ታጥቀን መቆም ያለብን” ብለው በምሳሌ ለማስተማር ሞክረዋል።

“አንዳንዶች ችግር ይገጥመዋል ብለው እየጠበቁ ነው። እኔም ተዘጋጅቼ ነው የመጣሁት” በማለት ጠመንጃቸውን እያሳዩ መድረክ ላይ ቀልድ ጣል አድርገዋል።

ፓስተሩ ከምእመኑ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ስለሚሰበስቡ ሰባኪያን በማንሳት “ከእንዲህ አይነቶች እራሳችንን ለመጠበቅ መታጠቅ አለብን” በማለት ጠመንጃቸውን ለምሳሌው ተጠቅመውበታል።

በናይጄሪያ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ሕጋዊ የጦር መሳሪያ መታጠቅ የሚችለው በፖሊስ ባለሥልጣን ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ ነው።

በርካቶችን ያነጋገረው የፓስተሩ መሳሪያ ታጥቆ ለስብከት መገኘት ሲሆን፣ በተጨማሪም ጠመንጃው የፓስተሩ ይሁን የሌላ ሰው እንዲሁም በመሳሪያው ውስጥ ጥይት ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።

በናይጄሪያም ሆነ በሌሎች አገራት ውስጥ የሃይማኖት መምህራን በሚሰብኩበት ጊዜ የጦር መሳሪያ አንግተው ወደ መድረክ መውጣት የተለመደ ነገር አይደለም።

በዚህም ሳቢያ የፓስተር ኡቼ አይግቤ ድርጊትን የሚያሳየው ቪዲዮ በስፋት ከመሰራጨቱ ባሻገር በመላው ናይጄሪያ መነጋገሪያ ሆኗል።

የሰባኪውን ጠመንጃ ታጥቆ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣትን በተመለከተ ፓስተሩ ሲሰብኩበት የነበረው ቤተክርስቲያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ አልሰጠም።

ጠመንጃ አንጋቹ ሰባኪ በመሩት የእሁድ ሥነ ሥርዓት ላይ የተከሰተ ችግር ስለመኖሩ እና የጦር መሳሪያውን በተመለከተ ከፖሊስም ሆነ ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት የተባለ ነገር የለም።