እስራኤል በራፋህ የፈጸመችው ጥቃት እየተወገዘ ባለበት ወቅት ናታንያሁ ጦርነቱን እንደሚገፉበት ዛቱ

በራፋህ የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ እሁድ ሌሊት በፈጸመችው ጥቃት በርካታ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ውግዘት በተጠናከረበት ወቅት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ በጦርነቱ እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

በድንኳኖች በተጠለሉ ፍልስጤማውያን ላይ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 45 ሰዎች መገደላቸውን፣በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የከፋ ቃጠሎ እንደደረሰባቸው በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። በተጨማሪ በርካቶች ስብራት እና የከፉ ጉዳቶችን አስተናግደዋል።

በእስራኤል ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ናታንያሁ ጥቃቱን “አሳዛኝ ጥፋት ነው” ይበሉ እንጂ “ሁሉም ግብ ከመሳካቱ በፊት ጦርነቱን ስለማስቆም አላስብም” ሲሉ አክለዋል።

እስራኤል ሲቪሎችን ለመጠበቅ “የሚቻላትን ሁሉ ጥንቃቄ” ማድረጓ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑትን ላለመጉዳት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በአልጄሪያ ጥያቄ አቅራቢነት በራፋህ ጥቃት ላይ ለመወያየት ማክሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ይቀመጣል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ጥቃቱ “ከጦርነቱ ሸሽተው የተጠለሉ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል” ብለዋል።

"በጋዛ ውስጥ ምንም አስተማማኝ መጠለያ ቦታ የለም። ይህ አስፈሪ ጥቃት መቆም አለበት" ብለዋል።

ሐማስ መስከረም 26 ካደረሰው ጥቃት በኋላ ታግተው የተወሰዱ እስራኤላዊያን ቤተሰቦች አልፎ አልፎ በሰነዘሩት ተቃውሞ የኔታንያሁ ንግግር ተቋርጧል። አንዳንዶቹም ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለመመለስ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩን እየተቹ ይገኛሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በራፋህ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ንጹሐን ነዋሪዎችን ለቀው እንዲወጡ እና ተዋጊ ያልሆኑትን ላለመጉዳት የምንችለውን ያህል ብንጥርም ይህ አሳዛኝ ስህተት ተፈጥሯል" ሲሉ አክለዋል።

"ክስተቱን እየመረመርን ሲሆን መደምደሚያ ላይም እንደርሳለን። ምክንያቱም ይህ የእኛ ፖሊሲ ነው።" ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥቃቱን አውግዘዋል። እስራኤል በራፋህ ላይ የምታካሂደውን ጥቃት እንድታቆም የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ያስተላለፈውን ውሳኔ እንድታከብር የአውሮፓ ህብረት አሳስቧል። የሕብረቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፕ ቦሬል ደግሞ የእሑዱን ጥቃት “አሰቃቂ” ብለውታል።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቢያስተላልፍም እስራኤል በራፋህ የጀመረችውን ወረራ ለመቀጠል ዝታለች። ውሳኔው ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ህግን ባከበረ መልኩ እንዲካሄድ ክፍት አድርጎ ትቶታል ሲሉ ባለስልጣናት መናገራቸው ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ተርክ፤ “እስራኤል የምትጠቀመው የጦርነት ዘዴና መንገድ ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንዳልመጣ የሚጠቁም ሲሆን ይህም ለብዙ ሲቪሎች ሞት ምክንያት ሆኗል” ሲሉ ስለ ጥቃቱ ተናግረዋል።

ሐማስ ከወራት በኋላ በቴል አቪቭ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳኤል ጥቃት ከፈጸመ ከሰዓታት በኋላ ነው እስራኤል ራፋህ ላይ ጥቃት የፈጸመችው።

የእስራኤል ጦር ባለስልጣናት በራፋህ በተፈጸመው ጥቃት ሁለት የሐማስ ከፍተኛ አዛዦች መገደላቸውን አስታውቀው፤ በአካባቢው የሠላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉን በመጣራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በበኩሉ የአየር ጥቃቱ ከመሐል ራፋህ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ታል አል ሱልጣን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋም አቅራቢያ በተፈናቀሉ ሰዎች በተጠለሉባቸው ድንኳኖች ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል።

እሑድ ምሽት በታል አል-ሱልጣን አካባቢ የተቀረጹ ቪዲዮዎች የከፋ ፍንዳታ እና ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ እንደነበር አሳይተዋል።

“የኩዌቲ የሰላም ካምፕ 1” ከሚል ባነር አጠገብ በርካታ ድንኳኖች ሲቃጠሉ፤ እንዲሁም እርዳታ ሰጪ ሠራተኞች እና ነዋሪዎች አስከሬኖች ይዘው ሲወጡ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።

ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ጥቃቱን ተከትሎ ከተቋማቱ በአንዱ ቢያንስ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 28 አስከሬኖችን ተቀብሏል።

ቃጠሎን ጨምሮ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው 180 ፍልስጤማውያን ህክምና መስጠቱንም ገልጿል።

እስራኤል ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት ማለቷን ኤምኤስኤፍ ውድቅ አድርጎታል። “በራፋህ ውስጥ ‘አስተማማኝ ዞን’ እየተባለ በሚጠራው መጠለያ ጣብያ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት በጋዛ ለሚኖሩ ሲቪሎች ያለውን ፍጹም ቸልተኝነት ያሳያል” ሲል አክሏል።

አሜሪካ ምስሎቹን "ልብ የሚሰብር" ብትልም እስራኤል ግን ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት አጥብቃ ተናገራለች።

“እስራኤል ሐማስን የማጥቃት መብት አላት። በዚህም ጥቃት በእስራኤላዊያን ሲቪሎች ላይ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጠያቂ የሆኑ ሁለት የሐማስ ከፍተኛ አሸባሪዎችን መግደሏን እንረዳለን” የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

"እስራኤል ሲቪሎችን ለመጠበቅ ማንኛውንም ጥንቃቄ ማድረግ አለባት" ሲሉ አክለዋል።

የእስራኤል ባለስልጣናት ሰኞ ዕለት በራፋህ የተፈጠረውን ጉዳይ ለማወቅ ታች ላይ ታች ሲሉ ውለዋል። ይህ ዒላማውን በጠበቀ መልኩ የሚሰነዘር ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለ፤ ብዙዎችን አቆሰለ? እንዴት እሳት አስከተለ?

ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በራፋህ በፍልስጤማውያን ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልን ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴ እንድታቆም ማዘዙን ተከትሎ የዓለም ዓይን በሙሉ እሷ ላይ ማነጣጠሩን እስራኤል ታውቃለች። ጥቃቱን እንድታስረዳም ከፍተኛ ጫና ይደረግባታል።

ናታንያሁ በራፋህ “ሙሉ ድል” ለሚሉት ዘመቻ አሁን ቁርጠኛ በመሆናቸው እሁድ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ጥቃት ሃሳባቸውን ስለመቀየሩ እስካሁን ምንም ምልክት የለም።

ከእሑድ ምሽቱ አስደንጋጭ ክስተት በኋላ የእስራኤል የምድር ጦር ወደ ራፋህ ከተማ እየተቃረበ ነው።

የእሁዱ የአየር ድብደባ ግን ቀድሞውንም የተበላሸው የእስራኤል ምስል ላይ ሌላ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ በዘመቻው ለመቀጠል ያላትን አመክንዮም አጨናግፏል።

የእስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረችው መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሌ እና 252 ሰዎችን አግተው ወደ ጋዛ ከወሰዱ በኋላ ነው።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከ36 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በጥቃቷ መገደላቸውን እና ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።