አፍሪካውያንን ከጦጣ ጋር ያነጻጸሩት አውሮፓዊው አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሊደረጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
አፍሪካውያንን ከጦጣ ጋር ያነጻጸሩት በኬንያ የሮማኒያ አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሊደረጉ ነው።
ሮማኒያ አምባሳደር ድራጎስ ቲጋው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ጠርታ ይፋዊ ይቅርታዋንም አቅርባለች።
አምባሳደሩ አፍሪካውያንን ከጦጣ ጋር አነጻጽረውበታል የተባለውን ንግግር ያደረጉት ናይሮቢ ኬንያ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ሕንጻ ውስጥ ሚያዚያ 18/2015 ዓ.ም. ነው።
እንደ ኤአፍፒ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ አምባሳደር ቲጋዉ አንድ ጦጣ በመስኮት ከተመለከቱ በኋላ፤ “የአፍሪካ ቡድን ተወካዮች ሊቀላቀሉን” ሲሉ አፊዘዋል።
የዚህ አምባሳደር ንግግር ቀድሞ ይፋ የሆነው ሐሙስ ዕለት ካማዉ ማቻሪያ በተባሉ በኬንያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣን በሆኑት ግለሰብ ነው።
ማቻሪያ በትዊተር ገጻላቸው ላይ የአምባሳደሩን ንግግር ‘አጸያፊ’ ሲሉ ከገለጹት በኋላ የአምባሳደሩን ባህሪ ለመሸፋፈን ሙከራ ተደርጓል ሲሉ ወቅሰዋል።
አምባሳደሩ ለንግግራቸው በግለሰብ ደረጃ ይቅርታ ጠይቀዋል ቢባልም ከትናንት በስቲያ አርብ አፍሪካውያን ዲፕሎማቶች ይፋዊ ይቅርታ እንዲደረግ መጠለያቸውን የኬንያው ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎ የሮማኒያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ይቅርታውን ጠይቆ አምባሰደሩን ወደ ቡካሬስት ጠርቷል።
የሮማኒያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ስለክስተቱ ሪፖርት የደረሰው እየተጠናቀቀ ባለው ሳምንት መሆኑን ገልጾ አምባሳደሩን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ሂደቶችን ጀምሪያለሁ ብሏል።
“በዚህ ሁኔታ ተጸጽተናል፤ ለተጎዱት ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን” ይላል የአውሮፓዊቷ አገር የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ።
“የዘረኝነት ባሕሪም ሆነ አስተያየት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” ያለው መግለጫው የአምባሳደሩ ንግግር ሮማኒያ ከአፍሪካ አገራት ያላት ግንኙነትን እንደማያበላሽ ተስፋ እናደርጋለን ብሏል።
ሮማኒያ ምንም እንኳ ከአፍሪካ ጋር ያላትን አብዛኛውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በአውሮፓ ኅብረት አማካይነት በኩል የምትፈጽም ቢሆንም ግብጽን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የሁለትዮሽ የንግግድ ስምምነት አላት።
በኬንያ የሮማኒያ አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መታዘዛቸውን ተከትሎ የናይሮቢው መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የሮማኒያ መገናኛ ብዙሃን ግን አምባሳደሩ አጥብቀው ተችተዋል። መገናኛ ብዙሃኑ ሮማኒያ በአምባሳደሮቿ ምክንያት ስትዋረድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ይላሉ።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እአአ 2014 ላይ በአርሜኒያ የሮማኒያ አምባሳደር የነበሩት ግለሰብ አይሁዳውያንን የሚያንቋሽሽ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ሮማኒያ በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ መገደዷን አስታውሰዋል።












