ፈረንሳይ የአምስተርዳሙን ግጭት ተከትሎ ከእስራኤል ጋር ለምታደርገው ጨዋታ ጥበቃዋን አጠናክራለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአምስተርዳም የማካቢ ቴል አቪቭ ደጋፊዎች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ በፈረንሳይ እና እስራኤል ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን ጨዋታ ለመጠበቅ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች በፓሪስ ተሰማርተዋል።

የፓሪስ ፖሊስ አዛዥ ሎረን ኑኔዝ እንዳሉት ከሆነ 4 ሺህ መኮንኖች ለጥበቃ ይሠማራሉ። 2 ሺህ 500 ፖሊሶች በሰሜን ፓሪስ በሚገኘው ስታድ ደ ፍራንስ ሲሰማሩ፤ ቀሪዎቹ በህዝብ ማመላለሻ መስጫዎች እና በዋና ከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ይሠማራሉ።

ወደ አንድ ሺህ 600 የሚጠጉ የግል የጥበቃ ሠራተኞች በስታዲየሙ ይሠማራሉ። የአገሪቱ ከፍተኛ የጸረ-ሽብር ፖሊስ ክፍል ደግሞ የእንግዳውን የእስራኤል ቡድንን ይጠብቃል።

“ከፍተኛ ስጋት ያለው ግጥሚያ ነው። [ምክንያቱም] ከጂኦፖለቲካዊ አውድ አንጻር ከፍተኛ ውጥረት አለበት “ ብለዋል ኑኔዝ።

“የህዝብን ጸጥታ ለማደፍረስ የሚደረግ ሙከራን አንታገስም።”

ባለፈው ሐሙስ በኔዘርላንድስ በአያክስ እና ማካቢ ቴል አቪቭ መካከል የተደረገውን ግጥሚያ ተከትሎ በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ነው ሁለቱ ሀገራት የሚያደርጉት የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ጨዋታ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት።

80 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው ስታዲየም 20 ሺህ ተመልካቾችን ብቻ ያስተናግዳል። የእስራኤል መንግስት የሰጠውን ምክር በመከተል ከ100 የማይበልጡ የእስራኤላዊያን ደጋፊዎች ብቻ ወደ ፓሪስ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሌሎች የእስራኤል ደጋፊዎችም ግን ጨዋታውን ለመመልከት ሊሄዱ ይችላሉ።

የእስራኤል ደጋፊዎች በአምስተርዳም ጎዳናዎች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ በአውሮፓ ያሉ ፖለቲከኞች "የጸረ-ሴማዊነት መመለስን" አውግዘዋል።

የማካቢ ደጋፊዎችም ንብረት በማበላሸት፣ የፍልስጤምን ባንዲራ በመቅደድ፣ ታክሲዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር እና ፀረ-አረብ መፈክሮችን በማሰማት ተሳታፊ መሆናቸውን የከተማዋ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ በእስራኤል እና በጎረቤቶቿ መካከል የሚካሄደው ግጭት ወደ አውሮፓ የመዛመት አቅም አለው።

ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ የሰሜን አፍሪካ ተወላጅ የሆኑ በርካታ ሙስሊም ህዝቦች አሏቸው።

የአምስተርዳሙን ጥቃት ተከትሎ ከአውሮፓ አይሁዶች ጋር ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ በሚል ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሐሙሱን ጨዋታ እንደሚታደሙ ተናግረዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሼል ባርኒየ እና የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ፍራንሷ ኦላንድ እና ኒኮላስ ሳርኮዚም ይገኛሉ።

ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊት ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯቸዋል። በአካባቢው ያሉ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች ከቀትር በኋላ እንዲዘጉ ተነግሯቸዋል።

በሊቨርፑል እና በሪያል ማድሪድ መካከል እአአ በ2022 በተካሄደው የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ስታደ ፍራንስ የህግ ጥሰት ተከስቶ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የተካሄዱት የራግቢ ዓለም ዋንጫ እና የፓሪስ ኦሊምፒክ በሠላም ተጠናቀዋል።

ግራ ዘመሙ እና ከእስራኤል ጋር በሚደረገው ግጭት ለፍልስጤማዊያን እና ሊባኖስ ድጋፉን የሚሰጠው ፍራንስ አንባውድ (ኤልኤፍአይ) የተባለው የአገሪቱ ፓርቲ ጨዋታው እንዲሰረዝ ወይም ፕሬዝዳንት ማክሮን በስታዲየም አንዳይታደሙ ጠይቋል።

“የእኛ ፕሬዝዳንት የዘር ማጥፋት ወንጀል የምትፈጽም አገርን እንዲያከብር አንፈልግም” ሲሉ የኤልኤፍአይ ምክትል ኃላፊ ዴቪድ ጉይራ ተናግረዋል። እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል ክሱን መሠረተ ቢስ እና እጅግ የተዛባ ነው ስትል አስተባብላለች።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሬቴይሉ በበኩላቸው ጨዋታውን መሰረዝም ሆነ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ተገቢነት የለውም ብለው “ፈረንሳይ ጥላቻን ለሚዘሩ ሰዎች ቦታ አትሰጥም” የሚል መልዕክት አሰምተዋል።

በዩኤፋ ውድድር ከፈረንሳይ እና እስራኤል በተጨማሪ ጣሊያን እና ቤልጂየም በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ። በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ቡዳፔስት ላይ ፈረንሳይ እስራኤልን 4 ለ 1 አሸንፋለች።

ረቡዕ ምሽት የእስራኤል ደጋፊዎች ዝግጅት በፓሪስ እንዲከናወን ፍቃድ ከተሰጠው በኋላ ውጥረቶች ቀደም ብለው መፈጠራቸውን ማስረጃዎች ነበሩ። የቀኝ ዘመሙ አክራሪው የእስራኤል ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በዝግጅቱ ይሳተፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም በኋላ በቪዲዮ ብቻ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዝግጅቱ ጎን ለጎን የፍልስጤም ደጋፊ እና የጸረ-ዘረኝነት ድርጅቶች በዋና ከተማዋ ሰልፎችን አቅደው ነበር።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በጋዛ እና ሊባኖስ ውስጥ "አረመኔነትን በማስፋፋት" ማክሮን ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ በፕሬዝዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መካከል ያለው ግንኙነት ላለፉት ሳምንታት ወደ ከባድ ውጥረት ተሸጋግሯል።

“ሀገራቸው የተፈጠረችው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ በመሆኑ” ኔታንያሁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የተኩስ አቁም ጥሪን መቀበል አለባቸው ማለታቸው የፈረንሳይ አይሁዶችንም ጭምር አበሳጭቷል። ይህ አገላለጽ ለአገራቸው ነጻነት ሲዋጉ ሕይወታቸውን ላጡ አይሁዶች እንደ ስድብ ይቆጠራል ሲሉም በርካታ እስራኤላዊያን ተርጉመውታል።

በምስራቅ እየሩሳሌም በሚገኝ እና በፈረንሳይ በሚተዳደር ቅዱስ ቦታ ላይ ሁለት የፈረንሳይ ባለስልጣናት በእስራኤል ኃላፊዎች ለአጭር ጊዜ መታሰራቸው ፓሪስን አበሳጭቷል።

ማክሮን ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር በተያያዘ ያላቸው አቋም ወጥ አይደለም ተብሏል።