ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመኪና አደጋ የደረሰባቸው የሃሪ ኬን ልጆች 'ደህና' መሆናቸውን አባታቸው ገለጸ
ሦስት መኪናዎችን ባካተተ የመኪና አደጋ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት የሃሪ ኬን ሦስት ልጆች ደህና መሆናቸው ተገለጸ።
አደጋው የተከሰተው ሰኞ ዕለት በሙኒክ ከተማ አቅራቢያ ሲሆን የእንግሊዙ አምበል በቻምፒንስ ሊግ አርሰናልን ለመግጠም ከሙኒክ ጋር ለንደን ይገኝ ነበር።
የአካባቢው የበጎ ፈቃደኞች የእሳት አደጋ ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሦስቱ መኪኖች ተሳፍረው የነበሩት በሙሉ ከባድ ጉዳት ባለማስተናገዳቸው "በጣም ዕድለኛ" ናቸው ብለዋል።
የኬን ቃል አቀባይ “[ልጆቹ] ደህና ናቸው። ወደ ሆስፒታል የሄዱት ለመደበኛ ምርመራ ነው” ብለዋል።
የጀርመኑ ጋዜጣ ቢልድ እንዳስነበበው ከሆነ በወቅቱ አጥቂው ቡድኑ ከአርሰናል ጋር ለሚያደርገው የቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ወደ ለንደን አቅንቶ ነበር።
የባቫሪያን ፖሊስ እንዳስታወቀው አራት ሰዎችን የጫነ ሬኖ ተሽከርካሪ መታጠፊያ ላይ ሲደርስ ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት የሆናቸውን የኬንን ልጆች ከጫነ መርሴዲስ ጋር ተጋጭቷል።
በኋላም ሬኖው ከላንድሮቨር መኪና ጋር መጋጨቱ ታውቋል።
የባቫሪያን ፖሊስ አክሎም በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል የተወሰደች ሴትን ጨምሮ በሦስቱም መኪና አደጋው የደረሰባቸው ዘጠኝ ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የበጎ ፈቃደኞች የእሳት አደጋ መከላከያ ኃላፊ ዳንኤል “ሁሉም መኪኖች ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። የመጀመሪያው ያየነው ነገር ከሁሉም መኪናዎች የተጎዱት ሰዎች ብዙ መሆናቸውን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"መልካም የሆነው ዜናው ማንም ሰው ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም። ልክ አንገት ላይ የሚያጋጥም ዓይነት የተለመደ የመኪና አደጋ ህመም ያሉ ቀላል ጉዳቶች ናቸው” ብለዋል።
“ፈጣሪ ይመስገን ማንም ከባድ የተጎዳ አልነበረውም። ሁሉም ሰዎች እድለኞች ናቸው።”
ፖሊስ አደጋውን በማጣራት ላይ ይገኛል።
ኬን ቶተንሃምን ከለቀቀ በኋላ በ2023 ባየር ሙኒክን በአራት ዓመት ኮንትራት ተቀላቅሏል።
ኬን እና ባለቤቱ ኬት አራት ልጆች አሏቸው። የወራት ዕድሜ ያለው የመጨረሻው ልጃቸው መኪናው ውስጥ አልነበረም ተብሏል።
የኬን ቤተሰቦች ዝውውሩን ተከትሎ በለንደን ቢቆዩም ከወራት በፊት “የባቫሪያ ቤቨርሊ ሂልስ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደሚገኝ መኖሪያ ቤት መግባታቸው ተዘግቧል።