ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንግሊዝ ከ ዩክሬን፡ “የዩክሬናውያን ሕልም ዌምብሊ ላይ ድል ማድረግ ነው”
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች 400 ቀናት ሊሆን በተቃረበበት ወቅት ዩክሬናውያንን ተስፋ የሚሰጣቸው አንድ ነገር እግር ኳስ ሆኗል።
ዛሬ በዕለተ ሰንበት፤ ዩክሬን በግዙፉ ዌምብሊ ስታድየም በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ እንግሊዝን ትገጥማለች።
ዩክሬን በጥሎ ማለፍ በዌልስ ተሸንፋ ከኳታር የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆኗ ይታወሳል።
እግር ኳስ አሁን ለዩክሬናውያን ከውጤትም በላይ ሆኗል። ቢያንስ ለሁለት ሰዓት ያህል ያሉበትን መከራ ረስተው የአገራቸው ልጆች ኳስ ሲያንሸራሽሩ ማየት የሚናቅ ነገር አይደለም።
“እግር ኳስ አሁንም ዩክሬን ውስጥ በጣም ተወዳጅ ስፖርት ነው። ሰዎች እያሳለፉ ያሉት ችግር የሚረሱበት መሣሪያ ነው” ይላል የቀድሞ የዩክሬን አጥቂ አንድሪ ሼቭቼንኮ።
“ሊጉ ቀጥሏል። አንዳንድ ክለቦች በአውሮፓ ውድድሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይሄ ትልቅ ነገር ነው” ሲል ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል።
ዛሬ መጋቢት 17/2015 ዓ.ም. እሑድ ምሽት 1፡00 በለንደኑ የዌምብሊ ስታድየም እንግሊዝ ዩክሬንን ስታስተናግድ እንዲመለከቱ 1 ሺህ ቲኬቶች ለዩክሬናውያን እና ላስጠጓቸው እንግሊዛውያን በነፃ ታድሏል።
ሌሎች 4200 ዩክሬናውያን ደግሞ በራሳቸው ቲኬት ገዝተው ጨዋታውን ለመታደም ተዘጋጅተዋል።
ግዙፉ ስታድየም ሙሉ በሙሉ ጢም ብሎ ሞልቶ 85 ሺህ ገደማ ተመልካቾች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በይፋዊ መግለጫም ሆነ በተለያየ መልኩ የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ጊዜያዊ አሠልጣኝ ረስላን ሮታን እና ተጫዎቾቹ ለዩናይትድ ኪንግደም ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
በ111 ጨዋታዎች ለአገሩ 48 ጎሎች ያስቆጠረው የባለን ዶር ተሸላሚው ሼቭቼንኮ ከሚኖርበት ለንደን ሰብዓዊ እርዳታ በማስተባበር ላይ ይገኛል።
ሼቭቼንኮ አሁንም ዩክሬን ውስጥ የቅርብ ዘመዶቹ እንደሚኖሩ ይናገራል።
‘ዩክሬናውያንን አንድ የሚያደርግ እምነት’
የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ማክሰኞ ለንደን የደረሰ ሲሆን፣ በብሬንትፈርድ መለማመጃ ሜዳ ላይ ልምምድ እያደረገ ቆይቷል።
ብሔራዊ ቡድኑ ባለፈው ሐሙስ ከንቦቹ (ብሬንትፈርድ) ጋር የወዳጅነት ግጥሚያም አድርጓል።
ዩክሬን ከስፔን እና ከፖርቹጋል ጋር በመጣመር የ2030 ዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ብታልምም ሞሮኮ ሁለቱን ጎረቤት አገሮች መቀላቀሏን ተከትሎ የዩክሬን ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ግልፅ አይደለም።
ባለው ጦርነት ምክንያት እና በአገሪቱ እግር ኳስ ማኅበር ውጥንቅጥ ምክንያት ዩክሬን የዓለም ዋንጫ ማዘጋጀት አትችልም የሚል ስጋት አለ።
ያም ሆነ ይህ በ1986 ባለን ዶር በማግኘት የመጀመሪያው ዩክሬናዊ የሆነው ኢጎር ቤላኖቭ በእሑዱ ጨዋታ ዩክሬን ይቀናታል የሚል እምነት አለው።
“ለእንግሊዝ እግር ኳስ ደጋፊዎች ይቅርታ እየጠየቅኩ ይህ ጨዋታ ከእነሱ በላይ እኛ ያስፈልገናል እላለሁ። የዩክሬናውያን ሕልም ዌምብሊ ላይ ድል ማድረግ ነው” ብሏል።
“እግር ኳስ ዩክሬንን አንድ የሚያደርግ እምነት ነው። ጦርነት ላይ ብንሆንም ወታደሮች፣ የጤና ባለሙያዎች እና በጎ ፈቃደኞች ለትንሽ ደቂቃም ቢሆን እረፍት ያሻቸዋል።”
በሌሎች የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ማልታ ከጣሊያን፣ ሉግዘምበርግ ከፖርቹጋል እንዲሁም ሰሜን አየርላንድ ከፊንላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።