ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል፡ ሱተን የዓመቱ ምርጥ ጨዋታ ያለውን ግጥሚያ ማን ያሸንፋል?
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አናት ላይ የተቀመጡት ሁለቱ ቡድኖች ቅዳሜ ይጫወታሉ። ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ሊቨርፑልን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ማን ያሸንፋል?
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ፍልሚያውን “የዓመቱ ምርጥ ጨዋታ” ብሎታል።
ኤርሊንግ ሃላንድ መሰለፉ አጠራጣሪ መሆኑ ውጤቱን ለመገመት ከባድ አድርጎታልም ብሏል።
ሱተን ይህንን ጨዋታ ጨምሮ ሁሉንም የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚከተለው ገምቷል።
ቅዳሜ
ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል
ሁለቱ ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ይመስለኛል።
ዳርዊን ኑኔዝን የያዘውና በሞሐመድ ሳላህ የሚመራው የሊቨርፑል አጥቂ መስመር ጨዋታ የሚቀይር መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።
ሊቨርፑል በመልሶ ማጥቃት ስጋት ሊፈጥር ቢችልም ሲቲ አጨዋወቱን አይቀይርም።
ሲቲዎች በሜዳቸው መጫወታቸው የበላይነት ይሰጣቸዋል።
ሃላንድ ተሰለፈም አልተሰለፈም በሜዳቸው መጫወታቸው ጠባብ ዕድል ይሰጣቸዋል።
ግምት፡ 2 – 1
በርንሌይ ከ ዌስት ሃም
በእርግጠኝነት የማይሰለፈውን ሚካይል አንቶኒዮን ጨምሮ ጃሮድ ቦዌን እና ሞሐመድ ኩዱስ መሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው።
በርንሌይ በሜዳው ሁሉንም ጨዋታዎችን መሸነፉ ሲጨመርበት ጨዋታውን ለመገመት ከባድ ያደርገዋል።
የቪሰንት ኮምፓኒ ቡድን በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ እንደመገኘቱ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ያስፈልገዋል።
ዌስት ሃም በጉዳት በሚያጣቸው ተጫዋቾች ምክንያት ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ሊያገኝ ይችላል።
ግምት፡ 1 – 1
ሉተን ከ ክሪስታል ፓላስ
ሉተን ላለመውረድ እየታገለ ቢሆንም በአሰልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ ስር ሆኖ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።
አሁንም እንደሚወርዱ ብገምትም በቅርቡ ካሳዩት አቋም አንጻር የመትረፍ ዕድል ይኖራቸዋል።
የፓላሱ አሰልጣኝ ሮይ ሆድሰን በዚህ ዓይነቱ ጨዋታ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ውጤት ላይ ያተኩራሉ።
ፓላስ ጎል የማይቆጠርበት ሲሆን አጥቂው ኤቤርቺ ኤዜ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል።
ግምት፡ 0 – 1
ኒውካስል ከ ቼልሲ
ኒውካስል እንደ አሌክሳንደር አይዛክ ያሉ ተጫዋቾች ከጉዳት ቢመለሱለትም ምን ያህል ብቁ ናቸው የሚለው ጥያቄ ያስነሳል።
ቼልሲም ክሪስቶፈር ንኩንኩን ከተቀያሪ ወንበር ሊያስጀምረው ይችላል። ቼልሲ ቢሻሻልም አሁንም ወጥ አቋም ማሳየት አልቻለም።
ከሲቲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ መሻሻል እንዳሳዩ ለማሳት ቢችሉም ለዚህ ጨዋታ ግን ዋስትና አይሆንም።
ግምት፡ 1 – 1
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ብራይተን
ብራይተን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በዚህ አካሄድ ሁሉንም ጨዋታቸውን 1 – 1 እገምታለሁ።
በውጤት ረገድ ብራይተን ከባለፈው ዓመት አንጻር አስተማማኝ ካለመሆኑም በላይ የሚቶማ መጎዳት ችግሩን ያባብሰዋል።
በዚህ ጨዋታ ብራይተን ያሸንፋል ብዬ ልገምት ባስብም ያለሚቶማ ግን ፎረስትም ዕድል አለው።
ግምት፡ 1 – 1
ሼፊልድ ዩናይትድ ከ ቦርንመዝ
በዚህ ጨዋታ ጎል እንደሚቆጠር እገምታለሁ።
ሼፊልዶች በድንቅ አቋማቸው ላይ ይገኛሉ። ቦርንመዞች ደግሞ ባለፈው ጨዋታ ኒውካስል ማሸነፍ ችለዋል።
ለመገመት የሚከብድ ጨዋታ ቢሆንም ዶምኒክ ሶላንኬ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ እንደሚሆን እገምታለሁ።
ግምት፡ 0 – 1
ብሬንትፎርድ ከ አርሰናል
ብሬንትፎርድ በሊቨርፑል 3 ለምንም ቢሸነፍም በጨዋታው አብዛኛው ደቂቃ ተፎካካሪ ሆኖ ቀርቧል።
በዚህ ምከንያት ለአርሰናል ቀላል ጨዋታ አይሆንም። ብሬንትፎርዶች በሜዳቸው ጠንካራ እና ለተቃራኒ ቡድን የማይመቹ ናቸው።
ሲቲ እና ሊቨርፑል ቀዳሚዎቹን ሁለት ደረጃዎች ይዘው ሲያጠናቅቁ አርሰናል ሦስተኛ ይሆናል።
ለዋንጫ ለመጫወት ከፈለጉ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይኖርባቸዋል።
ግምት፡ 0 – 1
እሑድ
ቶተንሃም ከ አስቶን ቪላ
ቶተንሃም ተጫዋቾችን በጉዳት እና በቅጣት ቢያጣም አጨዋወቱን አይቀይርም።
አስቶን ቪላ በኡናይ ኤምሪ ስር የተደራጀ እና የተዘጋጀ በመሆኑ ቶተንሃም እንዴት እንደሚቀርብ ለማየት ያጓጓል።
ቶተንሃም በኳስ ቁጥጥር በመብለጥ ለመጫወት ሲሞክር ቪላ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ይመርጣል።
አንድ አሸናፊ ቡድን መምረጥ ግድ ከሆነብኝ ቪላን እመርጣለሁ። ሆኖም ጨዋታው በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 2 – 2
ኤቨርተን ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ኤቨርተን በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት አሁን ላለመውረድ ቢፍጨረጨርም በሊጉ የመቆት ዕድል አለው።
ቅጣቱ ኤቨርተንን ሊያነቃቃ የመቻሉን ያህል ለማንቸስተር ዩናይትድም ዕድል ሊሆን ይችላል።
የሰሞኑ አቋማቸው ጥሩ ከመሆኑ አንጻር ተጫዋች በቀይ ካልወጣባቸው የማሸነፍ ዕድላቸው ትልቅ ነው።
ከውጤት አንጻር ማንቸስተር ዩናይትድ ከአምስት ጨዋታዎች አራቱን ቢያሸንፍም አቋሙ ግን ጥሩ አይደለም።
ሰማያዊዎቹ እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2 – 1
ሰኞ
ፉልሃም ከ ዎልቭስ
ፉልሃም ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ቢያገኝም ጥሩ አሰልጣኝ ስላላቸው ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገቡ አይመስለኝም።
ትልቁ ችግራቸው አጥቂውን አሌክሳንደር ሚትሮቪችን መተካት አለመቻላቸው ነው።
ዎልቭስም ምርጥ ባይሆንም ባለፉት ጨዋታዎች መሻሻል በማሳቱ ይህንን ጨዋታ ያሸንፋል።
ግምት፡ 0 – 2