ዋንጫው የት ይቀመጣል? የአውሮፓ ተሳትፎ እና የክሎፕ ስንብት - በሊጉ የፍጻሜ ጨዋታ ምን እንጠብቅ?

ታትሟል

ማንቸስተር ሲቲ የሊጉ አሸናፊ ለመሆን ከጫፍ ደርሷል።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ዌስትሃምን በማሸነፍ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ክብሩን በመድፋት አዲስ ክብረ ወሰን ይሰብራል።

አርሰናል በሜዳው ኤቨርተንን ካሸነፈ እና ሲቲ ነጥብ ከጣለ ደግሞ ከ20 ዓመት በኋላ ዋንጫው ወደ ኤምሬትስ ስታዲየም ያቀናል።

“ውጤቱን በራሳችን እንወስናለን። አርሰናል ነጥብ ይጥላል የሚለውን ተዉት። ኤቨርተን አንድ ነገር ይሠራል የሚለውንም እርሱት። አርሰናል ዓመቱን ሙሉ ተመልክቸዋለሁ” ብሏል ጋርዲዮላ።

“ትኩረታችን ከዌስት ሃም ጋር ባለን ጨዋታ ላይ ነው። በአዕምሮዬ ላይ የሚመላለሰው ዌስት ሃምን ማሸነፍ ብቻ ነው።”

“እያንዳንዱ እግር ኳስ ደጋፊ የሚፈልገው እስከመጨረሻው ጨዋታ የሊግ መርሃ ግብር የሚዘልቀውን ይህን መሰሉን ተአምር ነው” ያለው ደግሞ የአርሰናሉ ሚኬል አርቴታ ነው።

“በውቡ የዓለማችን ሊግ ፉክክሩ እስከመጨረሻ ይዘልቃል። ለዚህም ነው ከፍተኛ ፉክክር ያለበት የዓለማችን ሊግ የሆነው።”

“መገመት አለመቻሉ እንደሱስ ይሆናል። ብዙ ነገሮች ውጤቶችን በፍጥነት ይቀያይሩታል” ብሏል።

በመጨረሻው ቀን ጨዋታ የዩሮፓ ሊግ እና የዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ተሳታፊዎችም ይታወቃሉ።

ከዎልቭስ ጋር በሚደረገው ጨዋታ የርገን ክሎፕ ከሊቨርፑል ጋር የነበራቸው የዘጠኝ ዓመታት ቆይታ ይጠናቀቃል።

ሁለት ዋንጫዎች አንድ አሸናፊ

ዘንድሮ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ በመጨረሻው ዕለት መዳረሻው ሲታወቅ ለአስረኛ ጊዜ ነው።

ለዘጠኝ ዓመታት በአንፊልድ የነበራቸውን ቆይታ የሚያጠናቅቁት ክሎፕ ከዋንጫው ፉክክር ርቀዋል።

ከአርሰናል እና ከማንቸስተር ሲቲ አንዱ ዋንጫውን በመጨረሻው ቀን ያነሳል።

ከካይል ዎከር እና ማርቲን ኦዴጋርድ የትኛው ዋንጫውን ከፍ ያደርገዋል?

በኢትሃድ እና ኤምሬትስ ስታዲም መካከል ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት አለ። ስለዚህ ዋንጫው በየትኛው ስታዲየም ይቀመጣል?

ጨዋታው ሲጠናቀቅ ከአንዱ ስታዲየም ወደሌላኛው በሄሊኮፕተር አይጓጓዝም።

ሁለት ተመሳሳይ ዋንጫዎች ይዘጋጃሉ። አንዱ አሸናፊዎች ጋር ዓመቱን ሙሉ የሚቀመጥ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በፕሪሚር ሊጉ አስተዳዳሪ ዘንድ የሚቀመጥ ነው።

ለዋንጫ ማንሻ የሚዘጋጀው መድረክ በሁለቱም ስታዲየም ተመሳሳይ ይሆናል። የአሸናፊው ቡድን ስም ዋንጫው ላይ የሚጻፈው ከዋንጫ ስነ-ስርዓቱ በኋላ ነው።

ከሜዳሊያ አንጻር ደግሞ በሁለቱም ስታዲየሞች 40 በመዘጋጀታቸው ተጫዋቾች በሙሉ ስለሚሸለሙት ነገር ስጋት የለባቸውም።

አውሮፓ መድረክ ተሳትፎ

አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ያረጋገጠው አስተን ቪላ፤ ከማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር እንግሊዝን ወክሎ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን አረጋግጧል።

ቶተንሃም፣ ቼልሲ፣ ኒውካስል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በዩሮፓ ሊግ እና በዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ለመሳተፍ ይፎካከራሉ።

5ኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ቡድን በዩሮፓ ሊግ ይሳተፋል።

በ63 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስፐርስ መውረዱን ካረጋገጠው ሼፊልድ ዩናይትድ ጋር ይጨዋታል።

60 ነጥብ የያዘው ቼልሲ ደግሞ በሜዳው በርነመዝን ያስተናግዳል።

ማንቸስተር ሲቲ በኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ማንቸስተር ዩናይትድን ካሸነፈ በሊጉ 6ኛ ሆኖ ያጠናቀቅ ቡድን በቀጥታ የዩሮፓ ሊግ ላይ ይሳተፋል።

“ስድስተኛ ሆነን ማጠናቀቅ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው” ሲል የቼልሲ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ኮል ፓልመር ተናግሯል።

ቼልሲ በዘንድሮው የውድር ዓመት በአውሮፓ መድርክ ተሳትፎ አልነበረውም።

“መጀመሪያ ላይ ከነበረን ውጤት አንጻር አሁን ለአውሮፓ መድረክ መፎካከራችን በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን ያሳያል” ብሏል።

57 ነጥብ የሰበሰበው ኒውካስል ከብሬንትፎርድ ጋር ይጫወታል። ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ወደ ብራይተን ያቀናል።

ማንቸስተር ሲቲ የኤፍ ኤ ካፕን ካነሳ ሰባተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ቡድን በዩሮፓ ኮንፈርንስ ሊግ ይሳተፋል።

ቋፍ ላይ የሚገኘው ቡድን እና የወርቅ ጫማ

ሼፊልድ ዩናይትድ እና ብርንሌይ ከሊጉ መውረዳቸውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል። ሉተን በሒሳባዊ ስሌት ከሊጉ ያልወረደ ቢሆንም የመትረፍ ዕድሉ የማይመስል ነው።

ሉተን 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን 17ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኖቲንግሃም ፎረስት ጋር ያለው ልዩነት ሦስት ነጥብ ብቻ ነው።

ፎረስት በሉተን ተሸንፎ ሉተን ደግሞ ፉልሃምን በሜዳው ቢያሸንፍ፤ ሉተን ለመትረፍ ከ12 ጎል በላይ አስቆትሮ የጎል ልዩነቱን መብለጥ ይገባል።

ሌላስ ምን የሚወሰን ነገር አለ?

ኧሊንግ ሃላንድ የኮከብ ጎል አስቆጠሪነቱን እየመራ ሲሆን በተከታይነት ከተቀመጠው ኮል ፓልመር በአምስት ጎሎች ይበልጣል።

ሃላንድ የወርቅ ጫማውን ካሸነፈ ከእንግሊዙ አጥቂ ሃሪ ኬን ቀጥሎ በተከታታይ ሁለት ጊዜ ያሸነፈ ሁለተኛው ተጫዋች ይሆናል።

ኦሊ ዋትኪንስ ደግሞ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ቀዳሚ ነው።

በርካታ ጨዋታዎችን ጎል ሳያስተናግድ በማጠናቀቅ የወርቅ ጓንት አሸናፊ የሆነው የአርሰናሉ ዴቪድ ራያ ነው።