ቢሊየነሩ ኦሌግ ቲንኮቭ ዩክሬን መወረሯን በመቃወም የሩሲያ ዜግነታቸውን ሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በባንክ ዘርፍ የተሰማሩት ሩሲያዊው ቢሊየነር ኦሌግ ቲንኮቭ በዩክሬን ያለውን ጦርነት በመቃወም እና “የፑቲንን ፋሽስታዊነት” በማውገዝ የሩሲያ ዜግነትን አልፈልግም ብለዋል።
ቢሊየነሩ ቲንክኦፍ የተሰኘ በበይነ መረብ የሚሰራ በሩሲያ ትልቁ አበዳሪ የሆነ እና ከ 20 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉትን ባንክ ባለቤት ናቸው።
ባለሃብቱ በኢንስታግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በሰላማዊ ጎረቤቱ ላይ ጦርነት ከሚጀምር ፋሽስታዊ ሀገር ጋር አልተባበርም። ልትባበርም አልችልም” ሲሉ አስፍረዋል።
ጥቂት ሩሲያውያን ባለሃብቶች ሀገራቸው በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ በአደባባይ ተችተዋል።
ባለሃብቱ ዜግነታቸውን የሰረዙበት ወረቀት ‘ሶታ ቪዥን’ በተባለ ገለልተኛ የሩሲያ ዜና ምንጭ የትዊተር ገጽ ላይ ታይቷል።
በተጨማሪም ቢሊየነሩ በኢንስታግራም ገጻቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ዘልፈዋል።
ሆኖም ባለሃብቱ ያሰፈሯቸው ጽሁፎች ጠፍተዋል።
“ለኔ ይህንን ፓስፖርት ይዞ መቀጠል ያሳፍረኛል” ያሉት ኦሌግ ቲንኮቭ በዩኬ ሊኖሩ ይችላሉ የተባለ ቢሆንም እንደማንኛውም የሩሲያ ባለሃብት በዩኬ የማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
ሌሎች ታዋቂ የሩሲያ ባለሃብቶችም እኔን እንደሚከተሉኝ ተስፋ አድርጋለሁ። ይህ ደግሞ የፑቲንን አስተዳደር እና ኢኮኖሚ በማዳከም በመጨረሻ እንዲሸነፍ ያደርገዋል” ሲሉም አክለዋል።
ጨምረውም “የፑቲንን ሩሲያ ብጠላም ይህንን ጦርነት በግልጽ የሚቃወሙ ሁሉንም ሩሲያውያን እወዳለው” ብለዋል።
ባለሃብቱ ከዚህ ቀደምም የሩሲያ መንግሥትን በጠንካራ ቃላት ተችተው ነበር።
“የክሬምሊን ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ልጆቻቸውም በዚህ ክረምት ሜዲትራንያን አይሻገሩም። ባለሃብቶች የቀራቸውን ሃብት ለማዳን እየሞከሩ ነው” ብለው ነበር።
በኚህ እና በሌሎች ከፍተኛ ባለሃብቶች ምዕራባውያን የጣሉት ማዕቀብ፤ የጉዞ ማዕቀብ፣ የሃብት እገዳ እና የአውሮፕላን እና መርክብ ውርስን ይጨምራል።
የፕሬዝዳንት ፑቲን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሃያልነት ከመንግሥታቸው ጋር ግንኙነት ባላቸው ባለሃብቶች ላይ በእጅጉ የተመሰረተ ነው።
ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ወር ቲነኮቭ በቆጵሮስ ሚገኘውን ቤተሰባቸው ኩባንያ 35 በመቶ ድርሻ ሽጠዋል። ደርሻውን የገዙት ደግሞ ሩሲያዊው ባለሃብት ቭላድሚር ፖታኒን ሲሆኑ የአንድ ግዙፍ የማዕድን አውጪ ተቋም ሃላፊ ናቸው።
35 በመቶ ድርሻው የተሸጠው ኩባንያ በስሩ ባንክ፣ኢንሹራንስ እና የሞባይል ስልክ አምራችን ጨምሮ በርካታ ዘርፎችን አቅፏል።
ኒኮላይ ስቶርንስኪ የተባለ ሌላ በባንክ ዘርፍ የተሰማራ ሩሲያዊ ባለሃብት የሩሲያ ዜግነታቸውን መመለሳቸው ተዘግቦ ነበር።
ባለሃብቱ የብሪታኒያ ዜግንት ያላቸው ናቸው። ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ባወገዙበት የብሎግ ጽሁፋቸው ከዩክሬን ቤተሰቦቻቸው ጋር ግንኙነት እነዳላቸው ጠቁመዋል።
ከሳምንታት በፊት የእስራኤል እና ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላው ዩርኒ ሚሊነር የተባሉ ኢንቬስተር የሩሲያ ዜግነትን መተዋቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ሰውየው ሩሲያን እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ለቀው የወጡ ሲሆን በአሜሪካ እየኖሩ ይገኛሉ።












