ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዓይናቸውን ለምን እስያ ላይ ጣሉ?
“ሃይማኖተኛ አደለሁም። የማምነው ነገር የለኝም። ሊቨርፑል እምነቴ ነው። ለእኔ የሕይወቴ መስመር ነው።”
ይህን ያለው ቪጃይ ነው። ቪጃይ ውልደቱ ሲንጋፖር ነው። ከሊቨርፑሉ አንፊልድ ስታዲየም 11 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል። የሚወደው ቡድን ትውልድ ከተማውን እንዲጎበኝ እአአ ከ2011 ጀምሮ ሲጠብቅ ቆይቷል።
ይህ ግን የእሱ ብቻ ታሪክ አይደለም። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሊቨርፑል እና በክሪስታል ፓላስ መካከል የወዳጅነት ጨዋታ ተደርጓል። ከ50,000 በላይ ደጋፊዎች የሲንጋፖርን ብሔራዊ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተውታል።
ለሦስት ዓመታት የተጣለው የኮቪድ የጉዞ እገዳ ተነሳ። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖችም ለቅድመ-ውድድር ዝግጅት አድማስን እያቋረጡ ነው።
ጉዞዎቹ በገንዘብ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ እአአ በ2021 ወደ 56 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ እንዳጣ ክለቡ ይፋ አድርጎ ነበር። “ዋነኛው” ምክንያት ኮቪድ መስተጓጎል መሆኑ ተጠቅሷል። ከዚህ መካከል አንዱ በሕንድ ሊደረግ የነበረው የቅድመ ውድድር ዘመን ጉብኝት መሰረዙ ነው።
አሁን እገዳው ቀንሷል። ክለቦችም ቁጥር አንድ ወደሚሉት የገበያ ስፍራ እየጎረፉ ነው።
የሊቨርፑል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ቢሊ ሆጋን “እስያ በደጋፊዎች ብዛት ቀዳሚዋ መዳረሻችን ናት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የትኛውንም አውሮፕላን ተሳፍረህ ወደ ኤስያ ብትሄድ የሊቨርፑል ደጋፊዎችን ማግኘት ትችላለህ፣ ሲል አንድ ሰው የነገረኝን ማስታወስ እፈልጋለሁ። አንድ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ደጋፊያችን መገኛው እዚህ ነው። በእስያ ውስጥ ትልቅ ዕድል እንዳለ ይሰማናል።”
ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ
በዚህ ክረምት ማንቸስተር ዩናይትድ ፊቱን ወደ ታይላንድን እና አውስትራሊያን አዙሯል። ከሊቨርፑል እና ከክሪስታል ፓላስ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አከከናውኗል።
ቶተንሃም ሆትስፐር ወደ ደቡብ ኮሪያ አቅንቷል። ደቡብ ኮሪያ የክለቡ ከፍተኛ ኮከብ ግብ አግቢው ሶን ሄንግ ሚን አገር ነች።
ከስፖርት አንጻር እነዚህ ጉዞዎች ትርጉማቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለያዩ የሰዓት ዞኖች የሚደረጉ ረዥም በረራዎች፣ በከፍተኛ ሙቀት እና እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ልምምድ ማድረግን ያካትታል። ይህ ግን እንግሊዝ ለሚኖራቸው የአዲሱ የውድድር ዘመን ዝግጅት ጥሩ አይደለም።
የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “የምመርጠው ነገር አይደለም” ብለዋል።
“ሲጀምር እኔ አሰልጣኝ ነኝ። ለሁለት ሳምንት ኦስትሪያ ቆይተን በቀን ሁለት ጊዜ ብናሰልጥን ጥሩ ነበር።
“የደጋፊዎቻችን ቁጥር እስያ ውስጥ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ እናውቃለን። ወደ እነርሱ ቀረብ ማለት ጥሩ ነገር ነው።”
እንደ እውነቱ ከሆነ በእግር ኳስ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የከረመ ክርክር ነበር። ክርክሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ውሳኔ ያገኘ ይመስላል። ከፋይናንስ ጋር ያለው ወገን የበላይነት ይዟል።
በዚህ ዓመት የወጡ አዳዲስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም አቀፍ ጨዋታ አስተላላፊዎች ከፍተኛ ገቢ ያገኛል።
ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ከእንግሊዝ ገበያ ከሚገኘው የበለጠ ገቢ ይሆናል። በሚቀጥለው የውድድር ዓመት እስከ 2025 ባለው ጊዜ ከእስያ ገበያ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።
ስፐርስ በደቡብ ኮሪያ የወደጅነት ጨዋታ አድርጓል። ይህም ከሃገሪቱ ክለቦች ከተወጣጡ የኮከቦች ቡድን ጋር ተደረገ ሲሆን፣ የጨዋታው ትኬት በ25 ደቂቃ ውስጥ ተሸጦ ተጠናቋል። በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ስርጭት ያገኘ የስፖርት ዝግጅት ሆኗል።
ባንኮክ የሚገኙ የውድድሩ አዘጋጆች በማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል መካከል ለሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ የትኬት መነሻ ዋጋው 136 ዶላር አድርገዋል። በሲንጋፖር ርካሽ የተባለለት ቲኬት 107 ዶላር ተቸብችቧል።
እነዚህ ዋጋዎች ከእንግሊዝ የነጥብ ጨዋታዎች አንጻር እንኳን ውድ የሚባሉ ናቸው። ሆኖም የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ክለቦችን የመሳብ ጠንካራ አቅም አላቸው።
የሊቨርፑል ቃል አቀባይ “የእነዚህን የቲኬቶች ዋጋ እኛ አልወሰንም። እኛ የተወሰነልንን ክፍያ እንቀበላለን። እኛ ከትኬት ገቢ ምንም አይነት ድርሻ አንቀበልም" ብለው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእስያ ገቢ
ክለቦቹ ከእነዚህ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ምን ያህል እንደሚያገኙ አይታወቅም። ምክንያቱም መረጃው በጥብቅ ስለሚያዝ። ተንታኞች እንደሚሉት ግን ክፍያውን ለጉዞዎቹ ብቸኛ ምክንያት አድርጎ አያስቀምጥም። ለዚህ እንደምክንያት የሚቀመጠው የጉዞ እና የሠራተኞች ወጪዎች መኖራቸው ነው።
“በእውነቱ ከሆነ ቡድኖቹ ከቅድመ-ውድድር ጨዋታዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቀጥታ አያገኙም። ምናልባትም በአንድ ግጥሚያ ጥቂት ሚሊዮን ዶላር ቢገኝ ነው” ሲል የስፖርት ቢዝነሱ የእስያ-ፓስፊክ አርታኢ ኬቨን ማኩላግ ይገልጻል።
“ነገር ግን አንድ ትልቅ ዓላማ አለ። ይህም የስም ግንባታ እና በቀጣይ የቴሌቭዥን ሥርጭት ገበያውን በሚመራውና የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን በሚያስገኘው ገበያ ውስጥ መሳተፍ ነው። ትክክለኛው ገንዘብ ይህ ነው።”
ሊቨርፑል በሲንጋፖር በከተመበት ወቅት ከ240 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው አዲስ የማሊያ ስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ ስታንዳርድር ቻርተርድ ከተባለውና ትኩረቱን እስያ ላይ ካደረገው ባንክ ጋር ተደርሷል።
የእግር ኳስ ክለቦች የስፖንሰርን አቅማቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ የደጋፊዎችን መረጃ ሊያቀርቡላቸው ይችላሉ።
ለምሳሌ ማንቸስተር ዩናይትድ የደጋፊ ግንኙነት አስተዳደር (ሲአርኤም) ዳታቤዝ 50 ሚሊዮን መዝገቦችን እንደያዘ ይገምታል። ባለፈው ዓመት በማኅበራዊ ሚዲያው 176 ሚሊዮን አስፍሯል።
ይህም ለስፖንሰርሺፕ ገንዘብ፣ ስያሜ እና ለግብይት ክፍል የሚረዱ ከክለቡ ጋር የተመዘገቡ ወይም የተሳተፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን ጠቃሚ መረጃ ያስገኛል።
“የመጀመሪያው ትልልቅ ስፖንሰሮች የሚጠይቁት በደጋፊዎች ዙሪያ ያለውን መረጃ ነው” ሲል ማኩላግ ተናግሯል።
“ገንዘባቸውን ፈሰስ ከማድረጋቸው በፊት አንድ ክለብ ምን ያህል ደጋፊ እንዳለው፣ ዕድሜ፣ ወንድ፣ ሴት፣ የገቢ መጠን እና የመሳሰሉትን ነገሮች ማወቅ ይፈልጋሉ።”
የእንግሊዝ እግር ኳስን በገንዘብ በስፋት እንዲሰበሰብ ያስቻለው ግን የቴሌቭዥን ገቢ ነው።
ለዓመታት ሌሎች የስፖርት ሊጎች (የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጎችን ጨምሮ) ፕሪሚየር ሊጉን በቅናት ሲመለከቱ ኖረዋል። ወደ እስያ በማቅናት እነዚህ ሊጎች ቀዳሚ ናቸው።
የፕሪሚየር ሊጉ ፉክክር፣ ልዩ የሆነው የደጋፊዎች ባህል እና ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ጋር ያለው ትስስር ሊጉ በዓለም አቀፍ ደረጃ 3.2 ቢሊየን ተመልካቾችን በመሳብ በብዛት የታየ የስፖርት ሊግ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል።
ፕሪሚየር ሊግ እንደሚለው ግማሹ የዓለም ደጋፊ እና አንድ አራተኛው የቴሌቭዥን ተመልካቾች በእስያ ፓስፊክ ይገኛል። ይህ ሁሉ የሆነው ብዙ ጨዋታዎች በእኩለ ሌሊት እየተጠናቀቁም ነው።
እነዚህን ሁሉ ደጋፊዎች ይዞ ማቆየት ፈታኝ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይም ለወጣቱ ትውልድ በጣም ሰፊ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች እና የአኗኗር ዘይቤዎች አማራጮች መኖራቸው ዋነኛው ስጋት ነው።
የስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ፕሬዝዳንት የሆኑት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ባለፈው ዓመት “ወጣቶች በእግር ኳስ ላይ ፍላጎት የላቸውም። ራሳቸውን የሚያዘናጉባቸው ሌሎች መድረኮች አሏቸው” ማለታቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው።
ይህ አመለካከት የቴሌቭዥን ገቢ ውሎ አድሮ እየቀነሰ እንደሚሄድ ከተገመተው ትንበያ ጋር ተደማምሮ በአውሮፓ ከፍተኛ የእግር ኳስ ክለቦች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ኃላፊዎችን ደጋፊዎቻቸውን ለማሳተፍ አዲስ ውድድር መፈጠር እንዳለበት አሳምኗቸዋል።
አንደኛው ሃሳብ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ነበር። አምስት የእንግሊዝ ክለቦችን ጨምሮ ሁሌም ተሳታፊ በሚሆኑ ክለቦች የሚደረግ ውድድር ለማድረግ ያቀደ ነበር።
ይህም በዓለም ዙሪያ በተለይም በእስያ ውስጥ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎችን ታላሚ ያደረገ ነበር። እነዚህ ሁሌም ኃያል ቡድኖች እርስ በእርስ ሲፎካከሩ ማየት የሚፈልጉ ናቸው፤ ግን በጅምር ቀረ።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በዓለምአቀፍ ደጋፊዎች ዘንድ ያስነሳው ቁጣ እንዲሰረዝ ምክንያት ሆነ።
“የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ስለእስያ ግምት መያዝ የለባቸውም። ስለሚያገኙት እያንዳንዱ ዶላር መታገል ግን አለባቸው” ሲሉ በፈረንሳይ በኤምሊዮን ቢዝነስ ትምህርት ቤት የስፖርት ፕሮፌሰር የሆኑት ሲሞን ቻድዊክ ተናግረዋል።
“የእስያ ሸማቾች ብልህ፣ የተራቀቁ እና አስተዋይ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ እግር ኳስ በእስያ ደጋፊዎች መካከል መጠነኛ መለያየት እንዳለ ሊከራከሩ ይችላሉ። ስለዚህ ክለቦች እስያን በቀላሉ እንደሚቆጣጠሩት በማሰብ እብሪተኛ ወይም የዋህ እንዳይሆኑ ይመከራሉ።"
ቻድዊክ አክለውም የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች በውጭ አገራት ሊደረጉ ይችላሉ ተብሎ በ 2008 ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው ሃሳብ ከአጭር እስከ መካከለኛ ባለው ጊዜ የማይሳካ ነው። ጉዳዩ ግን በድጋሚ ሊታይ ይችላል።
ወደ ሲንጋፖር እንመለስ፤ ቪጃይ ሸሚዙን አውልቆ ጀርባውን ያሳያል። በንቅሳት ተዥጎርጉሯል። የሊቨርፑል ስም እና ክለቡ በታሪኩ ዋንጫ ያገኘባቸው ዓመታትን ተነቅሷል። ስለ ወደፊቱም ቢሆን ብሩህ ተስፋ ሰንቋል።
“አባቴ የሊቨርፑል ደጋፊ ነበር። ከሴት ልጆቼ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረግኩት ነገር የሊቨርፑል ማሊያን ለእነሱ ማልበስ ነበር። እመኑኝ ይህ በትውልዶችን ቅብብል ይቀጥላል” ሲል ያጠናቅቃል።