ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሲሪላንካው መሪ ከከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ ስልጣን ለቀቁ
ለወራት ከዘለቀ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ አገር ጥለው የሸሹት የሲሪላንካው መሪ ጎታባያ ራጃፓክሳ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ይፋ አደረጉ።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ለአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ በኢሜይል መልዕክት ማስታወቃቸውም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ ከሁለት ቀናት በፊት ከባለቤታቸው እና ከሁለት የደኅንነት አባላት ጋር ወደ ማልዲቭስ ደሴት በጦር አውሮፕላን መሸሻቸው ይታወሳል።
ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 7 ደግሞ ሲንጋፖር መግባታቸው ሪፖርት ተደርጓል።
የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፤ ራጃፓክሳ ለሲንጋፖር መንግሥት የጥገኝነት ጥያቄ አለማቅረባቸውን ገልጸዋል።
የፕሬዝደንቱን ሽሽት ተከትሎ የሲሪላንካ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሪሜሲንግ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመው ነበር። የ73 ዓመቱ ፕሬዝዳንት አዲስ በሚመጣ መንግሥት ለእስር እንዳይዳረጉ በመስጋት ስሪላንካን ጥለው ከመውጣታቸው በፊት ስልጣናቸውን መልቀቅን አልመረጡም ነበር።
ራጃፓክሳ መንበራቸውን መልቀቃቸው ለበርካታ አስርት ዓመታት በአንድ ቤተሰብ አባላት ተይዞ የነበረውን ሥልጣን እንዲያበቃ ያደርገዋል። ሲሪላንካ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን በመጨረሷ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟታል። እንደ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና ምግብ የመሳሰሉ መሠረታዊ ቁሶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ተስኗታል። አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ውስጥ ለመግባቷ አገሬው በፕሬዝዳንቱን እና አስተዳደራቸውን ይተቻሉ። ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች ባለፉት ሳምንታት የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲሰያሰሙ ቆይተዋል። ከቀናት በፊት ከመላው አገሪቱ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች ወደ ፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት በኃይል ጥሰው ከገቡ በኋላ ፕሬዝደንቱ ሥልጣን እስኪለቁ ከመኖሪያ ቤቱ አንወጣም ብለው ነበር። ራጃፓክሳ ስልጣን መልቀቃቸው ከተገለጸ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሪላንካውያን ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።