ከኮቪድ ክልከላዎች ጋር በተያያዘ ቻይና ውስጥ የተነሳው ተቃውሞ መባባሱ ተነገረ

በቻይና ኡሩምቺ ግዛት በሚገኝ አንድ አፓርታማ ውስጥ 10 ሰዎችን የገደለው የእሳት ቃጠሎ በኮቪድ ክልከላ ምክንያት ነው በሚል የተነሳው ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉ ተነገረ።
በሻንጋይ ከተማ በውጪ ጋዜጠኞች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉት ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎጂዎችን ለማስታወስ እና የኮቪድ ክልከላዎችን በመቃወም ወደ ጎዳና ወጥተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩትም ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ስልጣን እንዲለቁ ሲጠይቁ ተደምጠዋል።
ብዙዎች ለመኖሪያ ሕንፃዎች መቃጠል ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የተጣለውን እገዳ ተጠያቂ አድርገዋል።
የቻይና ባለስልጣናት ይህ ምክንያት አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።
የኡሩምቺ ባለስልጣናት አርብ ዕለት ባልተለመደ መልኩ ይቅርታ ጠይቀው ግዴታቸውን ያልተወጡትን ለመቅጣትም ቃል ገብተዋል።
በሻንጋይ አንዳንድ ሰዎች ሻማ ሲያበሩ እና ለተጎጂዎች አበባ ሲያስቀምጡ ታይተዋል።
ሌሎች ደግሞ “ዢ ጂንፒንግ ከስልጣን ይውረዱ” እና “ኮሚኒስት ፓርቲ ከስልጣን ይውረድ” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ነጭ ባነሮችን ይዘው ታይተዋል።
በመንግስት እና በፕሬዚዳንቱ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ቀጥተኛ ትችት ከባድ ቅጣትን በሚያስከትልባት ቻይና እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች አልተለመዱም።
አንዳንድ ተቃዋሚዎችም ሰዎች በተሰበሰቡበት ጎዳና ላይ በተሰለፉት ፖሊሶች ላይ የስድብ ናዳ ሰንዝረዋል።
አንድ ተቃዋሚ ለአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ጓደኛቸው በፖሊስ ሲደበደብ ሁለቱ ደግሞ አስለቃሽ ጭስ ተረጭቶባቸዋል። ህዝቡ ተቃውሞውን ሲያሰማ ፖሊሶች ቆመው ሲመለከቱ የሚያሳዩ ሌሎች የተቃውሞው ቪዲዮዎችም ታይተዋል።

እሑድ ማለዳ በአካባቢው የነበረው ሁኔታየተረጋጋ ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባላት፣ የግል ጥበቃዎች እና ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በጎዳናዎች ላይ እንዳሉ ቢቢሲ ተመልክቷል።
ቅዳሜ ምሽት በበርካታ የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎችን ተቃውሞ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎች በበይነ መረብ ተሰራጭተዋል።
የተቃውሞ ሰልፎቹን የሚያሳዩ ቪዲዮዎቹን በገለልተኛ አካል ለማጣራት አስቸጋሪ ቢሆንም ብዙዎቹ ግን ከወትሮው በተለየ መልኩ በመንግሥት እና በመሪው ላይ ትችቶችን ሲሰነዝሩ ያሳያሉ።
ሰልፎቹ የቻይናን ዜሮ-ኮቪድ እርምጃዎችን በመቃወም በመንግሥት እና በፕሬዚዳንት ዢ ላይ የቀረቡ ተቃውሞችን ተከትለው የመጡ ናቸው።
ቻይና የዜሮ-ኮቪድ ስትራቴጂን የምትከተለው አንጻራዊ በሆነው ዝቅተኛ የክትባት ደረጃዋ እና አረጋውያንን ለመጠበቅ በምታደርገው ጥረት ነው።












