የዲሲው አውሮፕላን አደጋ ጥቁር ሣጥኖች ሲገኙ የሠራተኞች እጥረት ነበር በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ ተከፍቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዋሽንግተን ዲሲ ከወታደራዊ ሄሊኮፕተር ጋር ተጋጨው የመንገደኞች አውሮፕላን ጥቁር ሣጥኖች የተገኙ ሲሆን፤ በሠራተኞች ቁጥር እና አውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ በተወሰኑት ውሳኔዎች ዙሪያ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።
በአካባቢው ለሚበሩ ሄሊኮፕተሮች እና አውሮፕላኖች በተለምዶ ሁለት ሰዎች የአየር ትራፊክ ቁጥጥሩን የሚያከናውኑ ቢሆንም ግን በአደጋው ወቅት አንድ ሰው ብቻ እንደነበር የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው የሲቢኤስ ኒውስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
በሁለቱ አውሮፕላኖች ውስጥ የነበሩ 67 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን ክስተት በተመለከተ ባለስልጣናት ምርመራ ጀምረዋል።
የብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ (ኤንቲኤስቢ) የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በ30 ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል።
የበረራ ዳታ መቅጃ እና ኮክፒት ድምጽ መቅጃ የሆኑት ጥቁር ብላክ ሣጥኖች በበረራ ላይ ምን ችግር እንዳለ ፍንጭ ለመስጠት ይረዳሉ።
ሣጥኖቹ ወደ ኤንቲኤስቢ ቤተሙከራ እንደተወሰዱ እና ምርመራ እንደሚከናወን ሲቢኤስ ገልጿል።
በኒውዮርክ ታይምስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገበው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሰው ሃይል ቁጥር ጉዳይ "ያልተለመደ አይደለም" በሚል በፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ተገልጿል።
የፌዴራል መንግስት በኤፍኤኤ የሚገኙ የተወሰኑ ቁልፍ ቦታዎችን ለመሙላት ለዓመታት ሲታገል ቆይቷል።
በሬጋን ዋሽንግተን ብሔራዊ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሄሊኮፕተሮችን እና አውሮፕላኖችን የሚቆጣጠርበት አሠራር የተለመደ እና መመሪያዎችን ያልጣሰ ነው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ውሃ ጠላቂዎች ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለው በፖቶማክ ወንዝ የተጎጂዎችን አስከሬን በመፈለግ አሳልፈዋል።
የማፈላለግ ሥራው ሐሙስ ማምሻውን በአደገኛ ሁኔታ ምክንያት ተቋርጧል።
64 መንገደኞችን የጫነው የአሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላን ሦስት ሰዎችን ከጫነ እና ልምምድ ላይ ከነበረው የአርሚ ብላክ ሃውክ የጦር ሄሊኮፕተር ተጋጭቷል።
እስካሁን ከአውሮፕላኑ 27 እና ከሄሊኮፕተሩ ደግሞ አንድ አስከሬን ማግኘት ተችሏል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በዋይት ሃውስ የነበራቸውን መግለጫ በህሊና ጸሎት ጀምረዋል።
"ሁላችሁም የሚሰማችሁን ስቃይ መገመት ብቻ ነው የምንችለው። ልባችን ከናንተ ጋር በኃዘን ተሰብሯል " ብለዋል።
በቀድሞው የዴሞክራቶች አስተዳደር ኤፍኤኤ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን የሚቀጥርበት ዝቅተኛ መስፈርት ለግጭቱ መንስኤ መሆኑን ያለ ምንም ማስረጃ ጠቁመዋል።
ሐሙስ ምሽትም በአቪዬሽን ዘርፍ ውስጥ ብዝሃነትን፣ ፍትሃዊነትን እና ማካተትን (ዲኢአይን) የሚያስቆም ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ትራምፕ አዲስ የኤፍኤኤ ኃላፊን ለመሾም ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
የመንገደኞች አውሮፕላኑ ውስጥ ሁለት የበረዶ ሸርተቴ አሰልጣኝ ሩሲያውን ነበሩ።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "በአውሮፕላኑ ውስጥ ሌሎች ዜጎቻችን ነበሩ። የዋሽንግተኑ አደጋ አሰቃቂ ነው" ብለዋል።
"ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።"
ቻይናም በአደጋው ሁለት ዜጎቿ መሞታቸውን አረጋግጣ "የተሰማትን ሃዘን" ገልጻለች።
ቻይና "በፍለጋ እና በነፍስ አድን ሥራዎች ሂደት ላይ በፍጥነት እንዲከናወን፣ የአደጋውን መንስኤ በፍጥነት እንዲጣራ እና የክትትል እንዲደረግ" አሜሪካን መጠየቋን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጸዋል።












