ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ የሚሆኑባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ

ታትሟል

ዛሬ ማክሰኞ በቡዳፔስ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ምሽት 4፡31 ሲል የሴቶች የ1ሺህ 500 ሜትር ፍጻሜ ይካሄዳል። በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ትወከላለች።

ርቀቱን በ3፡54.93 በመጨረስ ምርጥ የግል ሰዓት ያላት ብርቄ ኃየሎም እንዲሁም 1ሺህ 500 ሜትርን 3፡55.08 በሆነ ሰዓት ያጠናቀቀችው ድርቤ ወልተጂ ተፋላሚዎች ናቸው።

አትሌት ብርቄ እና አትሌት ድርቤ በዛሬው ምሽት የፍጻሜ ውድድር ከኬንያ፣ ከኔዘርላንድስ እና ከእንግሊዝ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር ይጠበቃቸዋል።

በዚህ የፍጻሜ ውድድር ከሚጠበቁት የሌላ አገር አትሌቶች መካከል ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን እና የኔዘርላንዷ ሲፈን ሐሰን ይገኙበታል።

በአሁኑ ሰዓት በሴቶች አትሌቲክስ ቁጥር አንድ የሆነችው ኪፕዬጎን ዛሬ ከሚሳተፉ 12 ተወዳዳሪዎች በሙሉ ርቀቱን በአጭር ሰዓት አጠናቃለች።

የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮኗ ኪፕዬጎን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጣሊያን ላይ በነበረ የዳይመንድ ሊግ ውድድር 1ሺህ500 ሜትር ርቀትን 3፡49.11 በሆነ ሰዓት በመግባት በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበሯ ይታወሳል።

ሌላኛዋ ተጠባቂ አትሌት ሲፈን ሐሰን ነች፤ ሲፈን ቅዳሜ ማታ ተካሂዶ በነበረው የ10ሺህ ሜትር ፍጻሜ ላይ ውድድሩን ለመጨረስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሯት ወድቃ ከሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውጪ መሆኗ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

1ሺህ 500 ሜትር ርቀትን 3:51.95 በሆነ ሰዓት ያጠናቀቀችው ሲፈን፣ ዛሬ ማክሰኞ ምሽት 4፡31 ሲል በሚጀምረው ውድድር ሌላኛዋ ተጠባቂ አትሌቶች ናት።

በዚህ ርቀት ተሰላፊ ከሆኑት ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር በርቀቱ የተሻለ ሰዓት ያላት ሌላኛዋ እንግሊዛዊት አትሌት ላውራ ሚዩር ናት።

ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ላውራ 1ሺህ 500 ሜትር ርቀትን 3፡54.50 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ የቻለች አትሌት ናት።

የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል

ዛሬ ምሽት 4፡42 ሲል አትሌት ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ ለሜዳሊያ የሚፎካከሩበት ውድድር ይካሄዳል።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሞሮኮው ሱፊያን ኤል ባካሊ እና እንዲሁም ከኬንያውያን አትሌቶች ሳይመን ኮዬች እና አብረሃም ኪቢዎት ጠንካራ ፉክክር ይገጥማቸዋል።

ርቀቱን ባነሰ ሰዓት በመጨረስ የተሻለ ሰዓት ያለው አትሌት ለሜቻ ይህን ውድድር ሰፊ ግምት ተሰጥቶታል። አትሌት ለሜቻ ከሦስት ወራት ገደማ በፊት ፓሪስ ላይ በነበረ የዳይመንድ ሊግ ውድድር 3ሺህ ሜትር መሰናክልን 7፡52.11 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰንን ይዞ ይገኛል።

አትሌቱ ርቀቱን 7፡56.68 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ከቻለው ሞሮኮዋዊ አትሌት ጠንካራ ፉክክር ይጠበቀዋል።

ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጌትነት ዋለ ርቀቱን 8፡05.15 በሆነ ሰዓት የጨረሰ ሲሆን፣ ኬንያዊው ሳይመን ኮዬች ደግሞ 8፡04.19 የሆነ የግል ምርጥ ሰዓቱን ያስመዘገበ አትሌት ነው።