ዩክሬናዊያን ስልካችሁን ‘በደንብ ቻርጅ አድርጉ’ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዩክሬን ብሔራዊ የኃይል አገልግሎት ኩባንያ ዩክሬናዊያን ‘ስልካችሁን በደንብ ቻርጅ አድርጉ’ ሲል ምክር ሰጠ።
ዩክሬናዊያን ስልካቸውን ብቻም ሳይሆን ማንኛውንም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ የቤት ቁሳቁሶችን ‘አጥግበው ቻርጅ እንዲያደርጉ’ አሳስቧል።
ይህ የሆነው ሩሲያ የኃይል ጣቢያዎችን በሚሳኤል መደብደቧን ተከትሎ የኃይል አቅርቦት እየሳሳ በመምጣቱ ነው።
ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ሩሲያ በዩክሬን የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫዎችን ስትደበድብ ቆይታለች።
ይህም የሆነው ሩሲያን ከክሬሚያ የሚያገናኘው የአውሮፓ ረዥሙ ድልድይ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ በወሰደቻቸው ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃቶች ነው።
ትናንት ረቡዕ ሌላ ጥቃት በዩክሬን የኤሌክትሪክ ጣቢያ ላይ ከደረሰ በኋላ በአገሪቱ በቀን ለ4 ሰዓታት መብራት ይጠፋል።
የዩክሬን ዋናው የኃይል አቅራቢ ድርጅት፣ ኡክሬኔርጎ፣ ዜጎች ስልካቸውን፣ የኃይል ማከማቻ ሳጥን (ፖወር ባንክ)፣ ኃይል ቆጣቢ ባትሪዎችን በሙሉ ቻርጅ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ዩክሬናዊያን በቂ ውሃ እንዲያከማቹ ተነግሯቸዋል።
ብርድ መከላከል የሚያስችሉ ካልሲዎችና ብርድ ልብሶችንም ከወዲሁ እንዲያዘጋጁ ተመክረዋል።
ይህም ከዚህ ወዲህ እያየለ የሚመጣውን ውርጭ ለመቋቋም እንዲችሉ በሚል ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለነስኪ ከዚህ ቀደም ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት የአገሪቱን 30 ከመቶ ኃይል አቅርቦት ከጥቅም ውጭ እንዳደረገ አምነዋል።
ኡክሬኔርጎ የኃይል አቅራቢ ኩባንያ እንዳለው ደግሞ ባለፉት 10 ቀናት የደረሱ የሚሳኤል ድብደባዎች በኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ ያደረሱት ጉዳት ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ ባለፉት ስምንት ወራት ከደረሰው ጥቃት የከፋ ነው።
አሁን በዩክሬን ያለውን የኃይል እጥረት ለማመጣጠን ዜጎች በፈረቃ መብራት እንዲያገኙ እንደሚደረግም ኩባንያው በማኅበራዊ ገጹ ላይ አስፍሯል።
የኃይል መቆራረጡ አሁን ዋና ከተማዋን ኬዬቭን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የዩክሬን ክልሎችን አዳርሷል።
የሩሲያ ያለፉት 10 ቀናት የሚሳኤል ጥቃት ኪየቭንና ሌቪቭን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ላይ ያነጣጠረ ነበር።
ዩክሬናዊያን በተቻለ መጠን በተለይም ማታ ማታ ኃይል እንዲቆጥቡም ተመክረዋል።
አሁን የኃያሉን የውርጭ አየር ንብረት መግባት ተከትሎ ዩክሬናዊያን ማሞቅያ ለመለኮስ ይገደዳሉ። ይህም የኃይል ፍላጎት እንዲጨምር የሚያደርግ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሶላ ቮን ዶ ላየን ማንኛውም በሲቪል መሠረተ ልማት የሚደረግ ጥቃት የጦር ወንጀል ነው ብለዋል።
"እናቶችን፣ ልጆችን፣ ወላጆችን ከውሃና ከኤሌክትሪክ እንዲርቁ ማድርግ የሽብር ወንጀል ነው" ብለዋል ኡርሶላ ቮን ዶ ላየን።
ይህ በእንዲህ እያለ ስምንተኛ ወሩን እየደፈነ ባለው የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ በጦር ሜዳ ፈተና ገጥሟታል።
የዩክሬን ኃይሎች በርካታ ቦታዎችን በመልሶ ማጥቃት እያስመለሱ በመሆናቸው ፑቲን ከትናንት ጀምሮ በኬርሶን፣ በዛፖሬዥያን፣ በዶኔስክ እና በሉሃንስክ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አጽንተዋል።
እነዚህ አራት ትልልቅ ክልሎች ከዩክሬን ተወስደው የሩሲያ አካል መሆናቸው የታወጀው በፍጥነት ሕዝበ ውሳኔ ከተደረገ በኋላ ነው።
ይሁንና ሕዝበ ውሳኔ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና አልተሰጠውም።












