ፖሊስ የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ አዘጋጆች ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ደንገተኛ ብርበራ አካሄደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ ፖሊስ በመጪው ዓመት የሚካሄደው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ አዘጋጆች ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ድንገተኛ ብርበራ አደረገ።
በዋና መሥሪያ ቤቱ ላይ ድንገተኛ ብርበራ የተካሄደው ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ምርመራ መሆኑ ተገልጿል።
ቢቢሲ በኦሊምፒክ አዘጋጆቹ ጽህፈት ቤት ላይ ብርበራ የተካሄደው ለውድድር ዝግጅት ግንባታ ውሎች የተሰጡት ግልጽነት በጎደለው መልኩ ነው ከሚል ክስ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረድቷል።
የኦሊምፒክ አዘጋጁ ቡድን ቃል አቀባይ ፖሊስ ከሚያደርገው ምርመራ ጋር እየተባበርን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዛሬ ማክሰኞ የፀረ-ሙስና መርማሪዎች ከፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የኦሊምፒክ አዘጋጆች ዋና መሥሪያ ቤት እና ለውድድሩ ዝግጅት ግንባታ የሚያካሂደው ሶሊዴኦ የተባለ ተቋም መሥሪያ ቤት ድንገት ተገኝተዋል።
በፈረንሳይ የሚፈጸሙ የፋይናንስ ወንጀል የሚመረምረው ፒኤንኤፍ የተባለው ተቋም ከኦሎምፒክ አዘጋጁ እና ግንባታ ከሚያካሂደው ተቋም ጋር በተያያዘ በበርካታ ቦታዎች ድንገተኛ ፍተሻዎችን እያካሄደ እንደሆነ ገልጿል።
ፓሪስ 2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ዓመት ከሐምሌ 19 አስከ ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም. በፈረንሳይ መዲና ይደረጋል።
ዛሬ ማክሰኞ ፖሊስ ያደረገው ብርበራ ከቅርብ ወራት ወዲህ ፈረንሳይ በምታዘጋጀው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ፣ እንዲሁም በአገሪቱ አጠቃላይ ስፖርት ላይ ሌላ ጥቁር ነጥብ የጣለ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
ግንቦት ወር ላይ የፈረንሳይ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ብሪጀት ሄነሪኬስ ብዙ የዘርፉን ባለሙያዎች ባነጋገር ሁኔታ ሳይጠበቅ ከሥራቸው ተሰናብተው ነበር።
ሄነሪኬስ ሥራ ለመልቀቅ የወሰኑበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ካለው አለመግባባት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ በስፋት ታምኗል።
ከወራት በፊት ደግሞ የፈረንሳይ የእግር ኳስ እና ራግቢ ፌዴሬሽኖች ኃላፊዎች ከሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ በገዛ ፍቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ለቅቀው ነበር።












