የኒው ዚላንድ አብራሪ ኢንዶኔዢያ ውስጥ በአማጺዎች ታገት

አብራሪው ሲያበረው የነበረው አውሮፕላን ንብረትነቱ የሱሲ አየር መንገድ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የኒው ዚላንድ ዜጋ የሆነ አብራሪ በኢንዶኔዢያዋ ፓፑአ ግዛት በተገንጣይ አማጺዎች ታገት።

ኢንዶኔዢያ አሸባሪ ብላ የፈረጀችው የምዕራብ ፓፑአ ብሔራዊ ነጻ አውጭ ጦር ለእገታው ኃላፊነቱን ወስዷል።

አማጺዎቹ ለኢንዶኔዢያ መንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ አብራሪውን እንደሚገድሉ አስጠንቅቀዋል።

ፊሊፕ ማርቴንስ የተባለው አብራሪ የታገተው አውሮፕላኑን ተራራማ በሆነው አካባቢ ካሳረፈ በኋላ አማጺዎቹ አውሮፕላኑን በእሳት ካጋዩ በኋላ ነበር።

በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩት አምስት ተሳፋሪዎች ከእገታ በኋላ ተለቀዋል።

አማጺዎቹ ኢንዶኔዢያ ምዕራብ ፓፑአን ራሷን የቻለች ግዛት አድርጋ እውቅና እንድትሰጥ ይፈልጋሉ።

የአገሪቱ ፖሊስ ክስተቱን እየመረመርኩ ነው ይበል እንጂ አካባቢው ተራራማ በመሆኑ ምክንያት ወደ ስፍራው መሄድ የሚቻለው በአየር ብቻ በመሆኑ ለሎጂስቲክ አስቸጋሪ ነው ብሏል።

የአማጺ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኢንዶኔዢያ የምዕራብ ፓፑአ የነጻነት ጥያቄያቸው ምላሽ ለመስጠት ተነሳሽነት ካላሳየች እና ለድርድር ካልተቀመጠች አብራሪውን እንገድላለን ብለዋል።

የኒው ዚላንድ መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን እና በኢንዶኔዢያ ጃካርታ ያለው ቆንስላ ለአብራሪው ቤተሰብ ድጋፍ እያደረገ ነው ብሏል።

እንደ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ የሱሲ አየር መንገድ ንብረት የነበረው አውሮፕላን የተለያዩ ግብዓቶችን ጭኖ ነበር ወደ መዳረሻው የበረረው።

የፓፑአ ግዛት በሆላንድ ቅኝ ግዛት ስር ፓፑአ እና ምዕራብ ፓፑአ ተብላ ለሁለት ተከፍላ ትተዳደር ነበር። እአአ 1969 ግን በተባበሩት መንግሥታት አስተባበሪነት ብዙ ካጨቃጨቀ ምርጫ በኋላ ግዛቶቹ ወደ ኢንዶኔዢያ ተጠቃለዋል።

ከዚያ ወቅት ጀምሮ በኢንዶዢያ ጦር እና በተገንጣይ ኃይሎች መካከል ግጭቶች ያጋጥማሉ።

ፓፑኡ እአአ 1975 ላይ በአውስትራሊያ ነጻነቷን ከተሰጣት ፓፑአ ኒው ጊኒ ትለያለች።