ደፍሮኛል ያለችውን ግለሰብ የገደለችው አሜሪካዊት ታዳጊ ተፈረደባት

ታትሟል

ደፍሮኛል ያለችውን ግለሰብ በስለት ወግታ የገደለችው አሜሪካዊት ታዳጊ በአይዋ ፍርድ ቤት እስር ቢፈረድባትም በአምስት አመት አመክሮ እንድትታለፍ ወስኗል።

የ17 አመቷ ፓይፐር ሉዊስ ለገደለችው ዛቻሪ ብሩክስ ቤተሰብ 150 ሺህ ዶላር ቅጣት እንድትከፍል ተወስኖባታል።

ታዳጊዋ ግለሰቡን የገደለችው ከሁለት አመት በፊት በ15 አመቷ ነው።

ባለፈው ዓመት በሰው መግደል ወንጀልና ሆን ብሎ ጉዳት በማድረስ በቀረበባት ክስ ጥፋተኛ መሆኗን አምናለች።

 ሁለቱም ክሶች እስከ አስር አመት እስር ያስቀጣሉ።

ይህንን የአመክሮ ጊዜ ከጣሰች 20 አመት ልትታሰር ትችላለች።

ፓይፐር ማክሰኞ በፖልክ ግዛት ዳኛ ኤም ፖርተር ተፈርዶባታል።

በአመክሮዋ ውል መሰረት ዳኛው በአንድ መኖሪያ ቤት እንድትወሰንና የመከታተያ መሳሪያም ማጥለቅ እንዳለባት ወስነዋል።

“እርግጠኛ ነኝ! የሚቀጥሉት አምስት አመታት ህይወትሽ በማይስማሙሽ ህጎች የተሞላ ይሆናል። “ ያሉት ዳኛ ፖርተር “የጠየቅሽውን ሁለተኛ እድል አግኘተሻል፤ ሶስተኛ እድል አታገኝም” ብለዋታል።

ፓይፐር ደፍሮኛል ያለችውን ግለሰብ በመግደሏ ለቤተሰቡ የገንዘብ ቅጣት ለመፈጸም የተገደደችበትን አወዛጋቢ ሁኔታም አንስተው፣ በአዮዋ ህግ መሰረት “ፍርድ ቤቱን ይህን ብያኔ ከማሳለፍ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም” ብለዋል።

“መንፈሴ እንዲሰበር ቢደረግም አሁንም መነሳቴ አይቀርም። እንጠራራለሁ፣ እነሳለሁ፣ አድጋለሁ” ስትል ፓይፐር ካዘጋጀችው መግለጫ ላይ እንዳነበበች አሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

“ከጥቃት የተረፍኩኝ” ነኝ ስትልም አክላለች።

በቤት ውስጥ የሚደርስባትን ጥቃት አምልጣ በኮሪደሮች (መተላለፊያዎች) መተኛት የጀመረች ሲሆን አንድ ግለሰብም ወደ ቤቱ ካስጠጋት በኋላ ለሌሎች ግለሰቦች ለወሲብ ሲሸጣት ነበር።

ከመካከላቸው አንዱ የ37 አመቱ ዛቻሪ ሲሆን በተደጋጋሚ እንደደፈራትም ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።

ታዳጊዋ በአውሮፓውያኑ 2020 በአይዋ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ዴስ ሞይንስ በሚገኝ አፓርታማ ውስጥ ከ30 በላይ ጊዜ በስለት ወግታ ገድላዋለች ። ፓይፐር ገና የ15 አመት ታዳጊ ነበረች።

ፓይፐር ወንጀል መፈጸሟን ብታምን ድርጊቷን ግን ተከላክላለች።

"የሰው ህይወት ነጥቄያለሁ።የዛን ቀን አላማዬ የአንድን ሰው ህይወት ለማጥፋት አልነበረም። በአእምሮዬ ምንም ደህንነት እንደሌለኝ ተሰምቶኝ ነበር እናም አደጋ ላይ እንዳለሁ ተሰማኝ ለዚያም ነው ይህንን ድርጊት የፈጸምኩት” ብላለች።

ፖሊስ እና አቃብያነ ህግ ፓይፐር መደፈር እንደተፈጸመባትና ለወሲብ ንግድም እንደተጋለጠም አምነዋል። ነገር ግን አቃቤ ህግ ፓይፐር በወቅቱ ተኝታ እንደነበርና ስጋት ተደቅኖባት እንዳልነበር ተከራክሯል።