ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሰናል ቪላን አሸንፎ በመሪነቱ ይቀጥላል? ወይስ ዕድሉን ለሊቨርፑል እና ሲቲ አሳልፎ ይሰጣል?
የ33ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናሉ።
ቅዳሜ 6 ጨዋታዎች ሲከናወኑ፣ እሑድ ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ቀሪው የቼልሲ እና የኤቨርተን ጨዋታ ሰኞ እንዲከናወን መርሃ ግብር ወጥቶለታል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የእነዚህን ጨዋታዎች ግምት እንደሚለተው ሰጥቷል።
ኒውካስል ከ ቶተንሃም
ጎሎች የሚቆጠሩበት ድንቅ ጨዋታ እንደሚሆን እጠብቃለሁ።
ኒውካስል በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ክፍ ብሎ ለመጨረስ መነሳሳት እንዳለው ባለፈው ሳምንት ዌስት ሃምን ከኋላ ተነስቶ በማሸነፍ አሳይቷል።
ቶተንሃም ደግሞ በቀጣይ የውድድር ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ አቻ ለመለያየት አይጫወትም።
ግምት፡ 2 - 3
ብሬንትፎርድ ከ ሼፊልድ ዩናይትድ
መውረዱ አይቀሬ ቢመስልም ሼፊልድ ዩናይትድ እስከመጨረሻው ድረስ መፋለሙን ይቀጥላል።
ባለፈው ሳምንት ከቼልሲ ጋር አቻ መውጣት ቢችሉም አሁን ደግሞ ለማሸነፍ ትኩረት ያደርጋሉ።
ብሬንትፎርድ ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ቢወጣም ከሊጉ አለመውረዱን ወደማረጋገጥ እየተቃረበ ነው።
በዚህ ጨዋታም ከሼፊልድ ዩናይትድ የተሻለ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ስላላቸው ሦስት ነጥቡን ያሳካሉ።
ግምት፡ 2 - 0
በርንሌይ ከ ብራይተን
በርንሌይ በሊጉ ለመቆየት ከስድስት ጨዋታዎች አራቱን ማሸነፍ አለበት። ቡድኑ እስካሁን ካደረጋቸው 32 ጨዋታዎች አራቱን ብቻ ማሸነፉ ሲታይ ይህ የሚሳካ አይመስልም።
ከዚህ ጨዋታ ግን ነጥብ ሊያገኙ ይችላሉ።
ቪንሰንት ኮምፓኒ ካለፉት 6 ጨዋታዎች ቢያንስ አንዱን ማሸነፍ እንዳላቸው ቢገልጽም በዚህ ጨዋታም ሦስት ነጥብ የሚያሳኩ አይመስልም።
ግምት፡ 1 -1
ማንቸስተር ሲቲ ከ ሉተን
ሲቲ ይህን ጨዋታ በማሸነፍ በሊጉ መሪዎች ላይ ጫና የሚፈጥርበት ዕድል ይሰጠዋል። ሉተን ግን በቀላሉ እጅ አይሰጥም።
ባለፈው ሳምንት ከኋላ በመነሳት ቦርንመዝን ማሸነፋቸውም መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል።
ሲቲ በድንቅ ብቃቱ ላይ ባይሆንም ሉተን ግን ይቀላቸዋል።
ግምት፡ 3 - 0
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ዎልቭስ
ባለፈው ሳምንት በቶተንሃም ለተሸነፈው ፎረስት ይህ አስፈላጊ ጨዋታ ነው።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ቢያሸንፉም ዎልቭሶች ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ድረስ የተስተካከለ ቡድን አላቸው።
የዎልቭሱ አሰልጣኝ ጋሪ ኦኒዬል ባለፈው ሳምንት ከዌስት ሃም ጋር ባለቀ ሰዓት የተሻረባቸው የማሸነፊያ ጎል አሁንም ድረስ ቢያንገበግባቸውም እኔ ግን ትክክለኛ ውሳኔ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 - 1
ቦርንመዝ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
የማንቸስተሩ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከብሬንትፎርድ፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑል ጋር የነበራቸውን ጨዋታ ማሸነፍ ነበረብን ይላሉ።
ከአቋማቸው አንጻር ግን የትኛውን ጨዋታ አይተው ነው ይህን አስተያየት የሚሰጡን ያሰብላል።
በሊቨርፑል ተበልጠዋል። ከብሬንትፎርድ ጋር ዩናትድ እድለኛ ሆኖ ነው አቻ የተለያየው። ከቼልሲ ጋር ደግሞ በተከላካይ ስህተት ባገኙት አጋጣሚ ነው ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉት።
ቦርንመዝ ኦልድትራፎርድ ላይ 3 ለምንም ያሸነፉ ሲሆን በዚህም ጨዋታ ማሸነፍ ይችላሉ።
ቴን ሃግ በሚቀጥለው ዓመት በማንቸስተር አይቆዩም።
ባላቸው ምርጥ ተጫዋቾች ምክንያት የማንቸስተርን ውጤት መገመት ቢከብድም በዚያ መንገድ መቀጠል ግን አይችሉም።
ግምት፡ 2 - 1
ሊቨርፑል ከ ክሪስታል ፓላስ
ከማንቸስተር ጋር ነጥብ እንደመጣላቸው እና ከባድ ጨዋታ ከፊታቸው በመኖሩ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ አለባቸው።
ሞህ ሳላህ ከጉዳት ከተመለሰ በኋላ እንደቀድሞው ጎል እያስቆጠረ አይደለም።
ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት ፓላሶች ነጥብ መሰብሰብ ቢገባቸውም አንፊልድ ላይ ግን ምንም አያገኙም።
ግምት፡ 3 - 0
ዌስት ሃም ከ ፉልሃም
የዘንድሮ ኮከብ ጎል አስቆጣሪያቸው ጃሮድ ቦዌን በጉዳት ከዚህ ጨዋታ ውጭ ሊሆን ይችላል።
ባለፈው ሳምንት ከፉልሃም ብዙ ጠብቄ የነበረ ቢሆንም በኒውካስል ተሸንፈዋል።
ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ቢመስልም ብዙ ጎሎች ይቆጠራሉ።
ግምት፡ 2 - 2
አርሰናል ከ አስቶን ቪላ
አርሰናል በቻምፒዮንስ ሊግ ከባየር ሙኒክ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ትችት ቢያስተናግዱም ያን ያክል መጥፎ አልነበሩም።
ቡካዮ ሳካ ፍጹም ቅጣት ምት ለማግኘት እግሩን ከማኑዌል ኑዌር ጋር ከማጋጨት ይልቅ ኳሱን ለማስቆጠር ቢሞክር መድፈኞቹ ማሸነፍ ይችሉ ነበር።
ይህ ለአርሰናሎች ከባድ ጨዋታ ነው። የቀድሞ አሰልጣኛቸው ኡናይ ኤምሬ ቡድን ሲያጠቃ አደገኛ ነው።
ቪላ ጎል ማስቆጠር ቢችልም መድፈኞቹን ማሸነፍ አይችሉም።
ግምት፡ 3 - 1
ቼልሲ ከ ኤቨርተን
ስለቼልሲ ለመገመት አሁንም ከባድ ነው።
ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ባይሸነፉም አራቱ አቻ ተለያይተዋል።
ኤቨርተን ባለፈው ሳምንት በርንሌይን ማሸነፉ ትልቅ ነገር ቢሆንም ይህንን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
ቼልሲ ገና እየተሠራ ያለ ቡድን ከመሆኑ አንጻር ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 1 - 1