ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፕል መተግበሪያ ክሪሚያን የሩሲያ አካል አርጎ ማሳየት ጀመረ
የሩሲያ ጦር ሃይል ክሪሚያን የተቆጣጠረው እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ነበር። ነገሩ በዓለም ሃያላያን አገራት መካከልም የተካረረ እሰጥ አገባን ፈጥሮ ነበር።
የሩሲያ መንግሥት አፕል በካርታው ላይ ክሪሚያ የሩሲያ አካል እንደሆነች አድርጎ ማሳየት አለበት የሚል ጥያቄ ባቀረበው መሰረት አፕልም ክሪሚያ የሩሲያ አካል እንደሆነች አድርጎ በካርታው ላይ ማሳየት ጀምሯል።
በዚህም መሰረት አንደ ሰው ሩሲያ ውስጥ ሆኖ የአፕል ካርታን ወይም የአየር ፀባይ መተግበሪያን ሲጠቀም አብላጫ ሕዝቧ ሩስኪ ተናጋሪ የሆነው ክሪሚያ የሩሲያ ክፍለ ግዛት ሆና ነው የምትታየው።
ከሌላ አገር ግን እነዚህ መተግበሪያዎች የሚያሳዩት ክሪሚያ የየትኛውም አገር ክፍለ ግዛት እንዳልሆነች ነው።
ክሪሚያ የሩሲያ ክፍለ ግዛት ሆና መታየት አለባት ሲል የሩሲያ ፓርላማ (ዱማ) ላለፉት በርካታ ወራት ከአፕል ጋር ሲነጋገር ቆይቷል።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል ክሪሚያን የሩሲያም የዩክሬንም ሳይሆን፤ የዚህ አገር ያልተባለች ግዛት አድርጎ ማሳየት እንደሆነ አቋሙ ሲገልፅ ቆይቷል።
ቢሆንም ግን በመጨረሻ አፕል በሩሲያ ፍላጎት ለመሄድ መስማማቱን የዱማው የደህንነትና ፀረ ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢ ቫዝሊ ፒስካሪዎቭ ተናግረዋል።
ክሪሚያን የዩክሬን አካል እንደሆነች አድርጎ መግለፅ በሩሲያ ሕገ መንግሥት ወንጀል እንደሆነ የአፕል ተወካዮች ተረድተዋል ብለዋልም ሊቀ መንበሩ።
አፕል ግን እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።