ኤፍቢአይ የዶናልድ ትራምፕን ቤት በርብሮ ምን አገኘ?

ሚሥጥራዊ ሰነድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካው የወንጀል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ፣ በዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት የተገኙ ሰነዶችን፣ ትራምፕ “የፍትሕ ሂደትን ለማሰናከል” መሞከራቸውን እንደሚጠቁሙ ገልጸዋል።

ማራ ላ ጎ በተሸኘው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቅንጡ የመኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኙት እነዚህ ሰነዶች የአገሪቱ ከፍተኛ ምስጢሮችን የያዙ ናቸው።

በተጨማሪም የተመረጡ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ተገኝተዋል።

የንጹሀን ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ከእነዚህ ሰነዶች መካከል የተወሰኑት እንደሚመረጡ የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ገልጿል።

ትራምፕ በበኩላቸው ምርመራው እየተመራ ያለው “የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ወሮበሎች ነው” ብለዋል።

ኤፍቢአይ የትራምፕን ቤት ለመበርበር የወሰነው ለምን እንደሆነ የሚጠቁሙ ሰነዶች ይፋ የሆኑ ሲሆን፣ ከሰነዶቹ ውስጥ የተወሰኑት ክፍሎች ግን አደባባይ እንዲወጡ አልተፈቀደም።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ እንዳለው በትራምፕ ቤት የተገኙት 11 ጥቅል ምስጢራዊ ሰነዶች ናቸው።

የፌደራሉ የምርመራ መሥሪያ ቤት (ኤፍቢአይ) ቤቱን ለመበርበር ፈቃድ ያገኘው “ማስረጃዎች፣ የኮንትሮባንድ ሰነዶች፣ የወንጀል ይዘት ያላቸው ሰነዶች እና በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሰነዶች በቤቱ ውስጥ አሉ” የሚል መተማመኛ ለፍርድ ቤት ካስገባ በኋላ ነው።

በተጨማሪም ትራምፕ “የፍትሕ ሂደትን ለማሰናከል” መሞከራቸውን የሚጠቁሙ ሰነዶች በቤቱ እንዳሉም ለፍርድ ቤት ተገልጿል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት የካቲት ላይ ከትራምፕ ቤት የሰበሰባቸው 15 ካርቶን የሚሞሉ ሰነዶች ምስጢራዊ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ ነው ኤፍቢአይ ምርመራ የጀመረው።

በምርመራው 25 የአገር ጥብቅ ምስጢሮችን ጨምሮ 148 ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸው ተገልጿል።

ኤፍቢአይ ካገኛቸው ሰነዶች መካከል የተወሰነው ክፍል ተቀንሶ የተቀረው ይፋ ሲደረግ እንደታወቀው፣ በሰነዶቹ ላይ ትራምፕ እና አጋሮቻቸውን የተመለከቱ ምሥሎች ተገኝተዋል።

ይህም ጉዳዩን ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ያደርገዋል።

ማራ ላ ጎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፍተሻ የተደረገበት ቅርጡው የትራምፕ መኖሪያ ቤት ማራ ላ ጎ

በአሜሪካ በጥብቅ የሚጠበቁ ምስጢሮችን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሥልጣን ሲለቁ ይዘው መሄዳቸው ቀላል ነገር ተደርጎ አይወሰድም።

ከእነዚህ ሰነዶች መካከል ከአሜሪካውያን እንዲሁም ከውጭ አገራት የስለላ ተግባር ጋር የተያያዙ ይገኙበታል።

ትራምፕን በተመለከቱ ከተከፈቱ ምርመራዎች ግንባር ቀደሙ ይህ ሊሆን ይችላል።

ከእነዚህ ሰነዶች የተወሰኑት ለውጭ አገራት ዜጎች ይፋ የማይደረጉ ናቸው።

“በጣም አሳሳቢው ነገር ምስጢራዊ ሰነዶቹ ከመገኘታቸው ባሻገር ከሌሎች ሰነዶች ጋር መደበላለቃቸው ጭምር ነው” ብሏል የምርመራ ቡድኑ።

ትራምፕ ምስጢር ማጋለጥን ጨምሮ ቢያንስ ሦስት የተለያዩ የፌደራል ሕግጋትን እንደጣሱ ተገልጿል።

ከሰነዶቹ 38 ገጾች 21ዱ ሙሉ በሙሉ እንዳይታዩ ተሰርዘዋል።

ይህም ንጹሀን ዜጎችን ላለመጉዳት፣ የፀጥታ ባልደረቦችን ለመጠበቅና እየተካሄደ የሚገኝ ምርመራን ላለማሰናከል ሲባል ነው።

በሰነዶቹ የተካተቱ ምስክሮች ማንነት ይፋ ቢደረግ እንግልት ሊደርስባቸው ይችላል።

ትራምፕ በበኩላቸው በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር አኮብኩበዋል።

ምርመራውን በተመለከተም ‘ትሩዝ ሶሻል’ የተባለው የግል ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

ቤታቸው እንዲበረበር የፈቀዱት ዳኛ ብሩስ ሬንሀርት “ቤቴ እንዲበረበር መፍቀድ አልነበረበትም። ሰውዬው ይጠላኛል” ሲሉ ተችተዋል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤት የሚያደርገው ቀጣይ ምርመራ ምናልባትም ለሕዝብ እና መገናኛ ብዙኃን ይፋ ላይደረግ ይችላል።

ይህ የሚደረገው የሰነዶቹ ይዘት በፍርድ ቤት ስለሚገለጽ ነው።

ተጨማሪ ምስክሮች ተጠርተው ፍርዱ በዝግ ከተከናወነ በኋላ ውጤቱና ውሳኔው በይፋ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።