ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖሊስ ለታዳጊ ልጅ ሞት ምክንያት የሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው እፅ በሕጻናት ማቆያ ክፍል ውስጥ አገኘ
የኒው ዮርክ ፖሊስ በሕጻናት ማቆያ ክፍል ወለል ሥር ከፍተኛ መጠን ያለው ‘ፌንታላይን’ እና ሌሎች አደገኛ እፆች እንዲሁም እፅን ለመውሰድ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ማግኘቱን ገለጸ።
በዚህ ክፍል ውስጥ ኒኮላስ ዶሚኒኪ የተባለ የአንድ ዓመት ልጅ በተኛበት በሽታ መልክ ከመጠን በላይ አደንዛዥ እፅ ሳይወስድ እንዳልቀረ በተጠረጠረ ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ ባለፈው ዐርብ አስታውቆ ነበር።
ከኒው ዮርክ ፖሊስ መሥሪያ ቤት የወጡ ፎቶዎችም በክፍሉ ውስጥ ቡናማ እና ነጭ ቀለም ባላቸው ዱቄቶች የተሞሉ በርካታ የፕላስቲክ ከረጢቶችን አሳይተዋል።
ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያካሄድኩ ነው ብሏል።
ፖሊስ እንዳለው ፌንታላይን የተባለው እፅ ሕይወቱ ያለፈው የአንድ ዓመት ሕጻን በተኛበት ክፍል ውስጥ ምንጣፍ ሥር ተደብቆ ነበር።
ሌሎች ሦስት ሕጻናትም አደገኛ የሆነውን እፅ ካሸተቱ በኋላ ሆስፒታል ገብተዋል።
ለህመም ከተዳረጉት ሕጻናት መካከል ከአንዱ የተወሰደ የሽንት ምርመራም እፁ በሰውነቱ መኖሩን አረጋግጧል።
የሕጻናት ማቆያው ባለቤት ግሬ ሜንዴዝ እና ተከራይ ካርሊስቶን አሴቬዶ ብሪቶ የተባሉት ሁለቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የማንሃተን ዐቃቤ ሕግ ዳሚየን ዊሊያምስ “ግለሰቦቹ የሕጻናት ማቆያን የአደንዛዥ እፅ ማከማቻ በመጠቀማቸው እና አራት ልጆችን መርዘው አንዱን ገድለዋል” በሚል ክስ እንደቀረበባቸው ተናግረዋል።
በኒው ዮርኩ የሕጻናት ማቆያ ለታዳጊው ሞት እና በሦስት ልጆች መመረዝ ክስ የቀረበባቸው ሁለቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም ቀሪ ዘመናቸውን በእስር ያሳልፋሉ ተብሏል።
ፖሊስ እንደሚለው ከማቆያ ቦታ የተገኘው አንድ ኪሎ ግራም ፌንታላይን 500 ሺህ ሰዎችን የመግደል አቅም አለው።
መርማሪዎችም አንድ ኪሎ የሚመዝን እፅ ለማሸግ የሚያገለግል መሣሪያ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የሕጻናት ማቆያው ባለቤት ሜንዴዝ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ በሕጻናት ማቆያው ውስጥ የባለቤታቸው የቅርብ ዘመድ በሆነው ተከራይ ብሪቶ እፅ መቀመጡን እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ከደኅንነት ካሜራዎች የተገኙ ምስሎች እና የስልክ ቅጂዎች እንደሚያስረዱት ሕጻናቱ ከታመሙ በኋላ ሜንዴዝ ለድንገተኛ አደጋ የጥሪ ማዕከል 911 ከመደወሏ በፊት ለባለቤቷ በርካታ ጊዜ ደውላለች።
ከዚያም ባለቤቷ በሥፍራው ደርሶ በርካታ የሽያጭ ከረጢቶችን ከሕጻናት ማቆያው ማውጣቱን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
እንደ አቃቤያነ ሕግ ከሆነ ሜንዴዝ በቁጥጥር ሥር ከመዋሏ በፊትም ከስልኳ ላይ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የጽሑፍ መልዕክቶችን አጥፍታለች።
በኋላ ላይ ግን ባለሥልጣናት የጠፉትን የጽሑፍ መልዕክቶች ድጋሜ ማግኘት ችለዋል።
ፖሊስ በክስ መዝገቡ ላይ የድርጊቱ ተባባሪ እንደሆነ የተገለጸውን ባለቤቷን እየፈለገ ነው።
ግለሰቡ ከአደጋው በኋላ አካባቢውን ለቆ ሲወጣ በካሜራ መታየቱን ፖሊስ አስታውቋል።
‘ፌንታላይን’ በክኒን መልክ ለሕመም ማስታገሻነት ተብሎ የሚዘጋጅ መድሃኒት 50 እጥፍ ከሄሮይን በላይ አደገኛ ሲሆን በአሜሪካ ከአደንዛዥ እፅ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እየጨመረ ላለው ሞት ምክንያት ተደርጎ ይቀርባል።
እአአ 2010 ላይ በአሜሪካ ከመጠን በላይ የሆነ አደንዛዥ እፅ ወስደው ከሞቱ 40ሺህ ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ፌንታላይን ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ ነበር።
በ2021 ደግሞ በአደንዛዥ እፅ ምክንያት 100ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 66 በመቶ ፌንታላይን ከመጠን በላይ የወሰዱ ናቸው።