የተባበሩት መንግሥታት በርካቶች አደገኛ ዕፅ በመርፌ መውሰዳቸው አሳሳቢ ሆኗል አለ

ታትሟል

የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው ጥናት በርካቶች አደገኛ ዕፅ በመርፌ እየወሰዱ መሆኑን አሳየ።

ዓለም አቀፍ የአደገኛ ዕፅ አጠቃቀምን እንዲጠቁም በሚል የተደረገው ጥናት ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች መበርከታቸውን አሳይቷል።

በፈረንጆቹ 2021 ለምሳሌ 13.1 ሚሊዮን ሰዎች አደገኛ ዕፅ በሲሪንጅ ወስደዋል።

ከዚህ ጥናት ቀደም ከነበረው ቁጥር 18 በመቶ ማሻቀብ ማሳየቱን የመንግሥታቱ የዕፅና ወንጀል ቢሮ ገልጧል።

እንደ ፌንታኒል እና ሜታምፌታሚን ያሉ ዕፆች የሕገ-ወጥ መድኃኒት ገበያውን እንደተቆጣጠሩት የተባበሩት መንግሥታት ገልጧል።

በምድራችን የዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር 23 በመቶ ሲጨምር ከዕፅ ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎች ደግሞ 45 በመቶ አሻቅቧል አሊያም 40 ሚሊዮን ደርሷል።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው ለአደገኛ ዕፆች ተጋላጭ የሆኑት የአእምሮ በሽታ ያለባቸው፤ ደከም ካለ ማሕበረሰብ የወጡና ወጣቶች ናቸው።

ምስራቅ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ በርካቶች በሲሪንጋ አደገኛ ዕፅ የሚወስዱበት ቦታ ሆኖ ተገኝቷል።

ፌንታኒል የተሰኘው በክኒና መልክ የሚመጣ መድኃኒት ሰሜን አሜሪካን እያዳረሰ እንደሆነ ይህ ሪፖርት ጠቁሟል።

ከ18 ሃገራት በተወሰደ መረጃ መሠረት ወንዶች በአምስት እጥፍ ቀድመው አደገኛ ዕፅ መጠቀም ይጀምራሉ። ቀጥሎ ሴት ጓደኞቻቸውን ወደ ዕፅ መጠቀም ይጎትቷቸዋል።

ዓለማችን በዕፅ ተጠቃሚ ብትሞላም ሕክምና ማግኘት የሚችለው ከአምስት ሰዎች አንዱ መሆኑን ድርጀቱ ገልጦ በተለይ ሴቶች የተለያየ ጋሬጣ እንደተደነቀረባቸው ያስነብባል።

የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎች ሕክምና የማያገኙበት ምክንያት ብዙና የተጠላለፈ ነው።

አንደኛው ኮቪድ-19 ነው ተብሏል። ቀጥሎ ደግሞ ሕጋዊ ቅጣት ይደርስብኛል ብሎ መፍራት ነው።

ማሕበረሰባዊ ነቀፌታን መሸሽ፣ እንዲሁም ልጆችን ከማሳደግ ልከለከል እችላለሁ የሚል ፍራቻ ብዙዎች ሕክምና እንዳይሹ አድርጓቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዕፅና ወንጀል ቢሮ አለቃ ጋዳ ዋሊ እንደሚሉት በአብዛኛዎቹ ሃገራት ሰዎች ሕክምና ማግኘት ሲገባቸው ይህ ሳይሆን ቀርቷል።

“አደገኛ ዕፅ የሚያዘዋውሩ ቡድኖችን ማደን አለብን። እኒህ ቡድኖች ግጭትና ዓለም አቀፍ ቀውስ ሲኖር ይመቻቸዋል። በተለይ ደግሞ ‘ሲንቴቲክ’ ዕፆቻን በማምረትና በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር ሰዎችን ክፉኛ እየጎዱ ነው” ብለዋል።