በዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ሊላኩ መሆናቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ መቱ

የተወሰኑ የዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎች ያርፉበታል የተባለ የሩዋንዳ ሆቴል
የምስሉ መግለጫ, የተወሰኑ የዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎች ያርፉበታል የተባለ የሩዋንዳ ሆቴል
ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም በስደተኞች ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ እንደሚላኩ ከተነገራቸው በኋላ የረሃብ አድማ ማድረጋቸውን ተናገሩ።

በሰሴክስ፣ ጋትዊክ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኘው ብሩክ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል የሚገኙ አስራ ሰባት ጥገኝነት ጠያቂዎች ውሳኔውን ተከትሎ ያደረባቸውን ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ለቢቢሲ አጋርተዋል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የዩኬ መንግሥት አንዳንድ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ እቅድ እንዳለው ያስታወቀ ሲሆን የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮም የስደተኞች ደኅንነት “ከሁሉም በላይ ወሳኝ ነው” ብሏል።

ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ወደ ሩዋንዳ ለመሄድ እንዲዘጋጁ የሚገልጸውን የማሳሰቢያ ወረቀት ዝርዝር ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሰኔ 1 ቀን የወጣ አንድ ሰነድ፣ ወደ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ዋና መዲና ኪጋሊ በቅርቡ እንደሚወሰድ የተለየና በብሩክ እስር ቤት የሚገኝ አንድ ጥገኝነት ጠያቂ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ማለት እንደማይችል ያሳያል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓትልም በመጀመሪያው በረራ ያለፈቃድ አገሪቷ ውስጥ የገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች እአአ ሰኔ 14 ወደ ሩዋንዳ እንደሚላኩ ተናግረዋል።

የብሔራዊ እና ድንበር ሕግ መውጣቱን ተከትሎ የአገሪቷ መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ደህንነቱ ወደተጠበቀ ሦስተኛ አገር- ሩዋንዳ እንደሚልክ ያስታወቀው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

በዚህም ሩዋንዳ፣ ከፈረንሳይ በጀልባ ኢንግሊሽ ቻናልን በማቋረጥ እና በሌሎች ሕገ ወጥ መንገዶች ዩኬ ለገቡ ስደተኞች ጥገኝነት ለመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቷታል።

ጥገኝነት ጠያቂዎቹን 7 ሺህ 240 ኪሎ ሜትር አቆራርጦ የመውሰዱ ውሳኔም ከአፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ጋር የተደረገው የ151 ሚሊየን ዶላር ስምምነት አካል ነው።

 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነገጋረውና የረሃብ አድማ ካደረጉ አስራ ሰባት ጥገኝነት ጠያቂዎች አንዱ የሆነው ግለሰብ፣ ለአምስት ቀናት የረሃብ አድማ ካደረጉ በኋላ ከውሃ ጋር ቀላቅለው የሚወስዱትን ስኳር ጠባቂዎች መስጠት ካቆሙ በኋላ አድማው ረቡዕ ምሽት መጠናቀቁን ገልጿል።

ዩኬ ውስጥ ቤተሰብ እንዳለው የሚናገረው አሊ፣ ከኢምግሬሽን ባለሥልጣናት ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት የረሃብ አድማውን እንዲቆም ለማድረግ ጥረት ባደረጉ ጊዜ ነበር።

“ለመጨረሻ ጊዜ ያነጋገሩኝ ‘ምግብህን ተመገብ ከዚያም በጥሩ ጤንነት ላይ ሆነህ አውሮፕላን መሳፈር ትችላለህ’ የሚል ነበር” ብሏል አሊ።

ግብጻውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጨምሮ የረሃብ አድማውን የመቱት ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ እንደሚሸኙ በአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ከተነገራቸው 100 ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል ይገኙበታል።

አንደኛው ቡድንም ሰኔ 14 ወደ ሩዋንዳ እንደሚሸኝ የሚገልጽ ደብዳቤ ረቡዕ ዕለት ደርሶታል።

ስደተኞቹ እንደሚሉት የብሩክ እስር ቤት ባለሥልጣናት፣ ካሜራ ያላቸው ስልኮችን የከለከሉ ሲሆን ዘመናዊ ስልኮቻቸውን በመቀማትም ኢንተርኔት አገልግሎት ማስጠቀም የማያስችል ስልክ ሰጥተዋቸዋል።

ቢቢሲ የጥገኝነት ጠያቂዎቹን ዝርዝር ሁኔታ የያዘና ወደ ሩዋንዳ ለመሸኘት የተዘጋጀ ሙሉ ቅጂ ደብዳቤውን ማግኘት ችሏል።

20 ገጾች ያሉት ደብዳቤው የተጻፈው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ነው።

ሆኖም አንደኛው ክፍል ላይ ብቻ ለጥገኝነት ጠያቂው የደብዳቤውን ይዘት ለማስረዳት አስተርጓሚ እንደተገኘ ይገልጻል። በዚህ ደብዳቤ ላይ ግን የግለሰቡ ስም በተደጋጋሚ በተሳሳተ መልኩ ነው የተጻፈው።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ጥገኝነት ጠያቂዎች የእነርሱን ፊርማ የሚጠይቀውን ሰነድ ዝርዝር በተጻፈበት እንግሊዝኛ ቋንቋ መረዳት ባለመቻላቸው ይዘቱ ምን እንደሚል እንዲነግሯቸው የቢቢሲ ዘጋቢዎችን ጠይቀዋል።

እስካሁን የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮው ለምን ያህል ሰዎች የሩዋንዳ መሸኛ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው አልገለጸም።

ይሁን እንጂ ኬርፎርካሊስ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ባለፈው ወር ውስጥ ወደ ዩኬ የገቡ 100 የሚጠጉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከዩኬ እንደሚባረሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብሏል።

ድርጅቱ እነዚህን ጥገኝነት ጠያቂዎች በመለየት ከ60 በላይ ለሚሆኑት ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።

የመኝታ ክፍል
የምስሉ መግለጫ, በሩዋንዳ ለጥገኝነት ጠያቂዎቹ ማረፊያ የተዘጋጀ የመኝታ ክፍል

በሶሪያ ውስጥ ለውትድርና አገልግሎት ሲፈለግ የነበረ ሶሪያዊ ስደተኛ  “ለመሞት ዝግጁ ነኝ። ወደ ሩዋንዳ ግን አልዛወርም” ብሏል።

ስደተኛው አክሎም “ወደ ሩዋንዳ እንደምንላክና እዚያም የአምስት ዓመት የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚሰጡን የሚገልጸውን ዜና ስሰማ ራሴን መምታት ጀመርኩ” ሲል የተሰማውን ገልጿል።

የረሃብ አድማውን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮው በሰጠው ምላሽ “ጤና እና ደኅንነት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው” በማለት “እራስን መጉዳት ወይም ራስን ማጥፋትን ለመከላከል እያንዳንዱን እርምጃ እንወስዳለን። በእያንዳንዱ ማዕከል ውስጥ ለዚህ ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት እና የግለሰቦችን ፍላጎት የመደገፍ ኃላፊነት ያለው ራሱን የቻለ የደኅንነት ቡድን አለ” ሲል አስረድቷል።

የረሃብ አድማ ከመቱት አስራ ሰባት ግለሰቦች መካከል አንዱ እንደነበር ለቢቢሲ የገለጸው ግብጻዊ፣  የረሃብ አድማ ከማድረጉ በፊት ከአገር ውስጥ ቢሮው ጋር አለመገናኘቱን ገልጿል።

“አገሬን ለቅቄ የወጣሁት በቤተሰብ አለመግባባት ነው። እዚህ ለመድረስ በሊቢያ በርሃ ባየሁት ስቃይ ምክንያት ለአዕምሮ ጤና ችግር ተዳርጌያለሁ” ሲልም ስደተኛው የጤና ስጋት እንዳለው ተናግሯል።

ሆኖም ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ የሚደረጉ በረራዎችን በተመለከተ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ “አሁን ሂደቱን ለማደናቀፍና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩን ሂደት ለማዘግየት ሙከራዎች እንደሚደረጉ እናውቃለን፤ ግን የእንግሊዝ ሕዝብ የሚጠብቀውን ለመስጠት አልታክትም፤ ሙሉ በሙሉም ቁርጠኛ ነኝ” ብለዋል።

በስደተኞች ሕግ ክፍል ውስጥ የሚሰሩት ስቲቨን ጋሊቨር አንድሪው በበኩላቸው መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎቹን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ሰኔ 14ን አይጠብቅም ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስቴቨን አክለውም “መንግሥት ይህንን እንዲፈጽም የሚፈቅደው ሕግ እስከ ሰኔ 28 ቀን 2022 ድረስ ተግባራዊ የሚሆን አይመስልም። ይህም እያደረጉት ያለውን ነገር ሊፈታተን ይችላል። እናም ያንን ያውቃሉ፤ ይጠብቃሉም” ብለዋል።